በሩስያ ምርጫ ቀለም ማፍሰስን ጨምሮ የድምጽ መስጫ ኮሮጆዎችን ያበላሹ ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ለሶስት ቀናት በሚደረገው የሩሲያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የድምጽ መስጫ ኮሮጆዎችን ያበላሹ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሩስያ ባለስልጣናት ተናገሩ።
ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በምርጫው የመጀመሪያ ቀን ዓርብ መሆኑም ተገልጿል።
የድምጽ መስጫ ኮሮጆዎች ውስጥ አረንጓዴ ቀለም ማፍሰስ፣ ኮሮጆዎቹን በእሳት መለኮስ እንዲሁም በምርጫ ጣቢያዎች አካባቢ ርችቶች መተኮስ ያጋጠሙ ክስተቶች መሆናቸውን የመንግሥት ሚዲያዎች ዘግበዋል።
የዘንድሮው የሩሲያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫም የቭላድሚር ፑቲን የስልጣን ዘመንን በስድስት ዓመታት እንደሚያራዝመውም እርግጥ ነው ተብሏል።
ሆኖም ባለስልጣናቱ የህግ አስከባሪ አካላት ሁኔታዎችን በጥንቃቄ እንዲከታተሉም ጠይቀዋል።
እስከ ነገ እሁድ ድረስ በሚካሄደው የሩሲያ ምርጫ ፑቲን ተቃዋሚዎች በሌሉበት ሁኔታ በመወዳደራቸው ውጤቱ አጠራጣሪ አይደለም ተብሏል። የመንግሥት ሚዲያዎችም በሞስኮ የመራጮች ቁጥር 23 በመቶ መድረሱን ዘግበዋል።
እነዚህ የምርጫ ኮሮጆዎችን ማበላሸት በአብዛኛው የተከሰቱት በሞስኮ፣ በደቡባዊቷ ሩሲያ ቮሮኔዝ እና በሰሜን ካውካሰስ ካራቻይ ቼርኬሽያ የምርጫ ጣቢያዎች መሆኑንም የመንግሥት የዜና ወኪል የሆነው ታስ ዘግቧል።
በሴንት ፒተርስበርግ የምርጫ አካባቢ አንዲት ግለሰብ ተቀጣጣይ ቦምብ ስትወረውር የሚያሳየውን ጨምሮ በምርጫ ጣቢያዎች ላይ ስድስት ክስተቶችን የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ትክክለኛነት ቢቢሲ አረጋግጧል።
ከነዚህም መካከል በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች በሚገኙ የድምጽ መስጫ ኮሮጆዎች ላይ ቀለም ፈሷባቸው ታይቷል።
በሞስኮ በሚገኝ የምርጫ ጣቢያ አንዲት ሴት ደማቅ አረንጓዴ ፈሳሽ በኮሮጆው ውስጥ ስታፈስም ተቀርጻለች። በሌላ የድምጽ መስጫ ጣቢያ ላይ ደግሞ በአንድ የእሳት ቃጠሎ ሲነሳ አሳይቷል።
ሩሲያ በወረራ በያዘቻቸው የዩክሬን አካበቢዎችም ምርጫ እንዲካሄድ አስገድዳለች።
ስካዶቭስክ በምትባለው አነስተኛ ከተማ በምርጫ ጣቢያ ፊት ለፊት በሚገኝ የቆሻሻ መጣያ ውስጥ ፍንዳታ እንደነበር እና ጉዳት እንዳላጋጠመ በሩሲያ የተሾሙ የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል።
የድምጽ መስጫ ኮሮጆዎችን በማበላሸት ቢያንስ ስምንት ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ቢሆንም እነዚህ የጥፋት ድርጊቶች ፑቲንን ለመቃወም የተሰነዘሩ ስለመሆናቸው ባለስልጣናቱ ያሉት ነገር የለም።
ነገር ግን በቴሌግራም ላይ የተለጠፉ አንዳንድ ቪዲዮዎች እንደሚያሳዩት በምርጫ ሳጥኖቹ ላይ ጥፋት ካደረሱት መካከል የተወሰኑት የዩክሬን ደጋፊ መፈክሮችን ሲያሰሙ ታይተዋል።
የሩሲያ የምርጫ ኮሚሽን ኃላፊ ኤላ ፓምፊሎቫ ድርጊቱን የፈጸሙትን ግለሰቦች “አጭበርባሪዎች” ሲሉ የወረፏቸው ሲሆን በድምጽ መስጫ ኮሮጆዎች ላይ ቀለም በማፍሰስ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥ ለገንዘብ ብለው እንዳደረጉት አምነዋል ሲሉ ተናግረዋል። ከነዚህም መካከል አንደኛው 100 ሺህ ሩብል (850 ዶላር) ቃል ተገብቶለት ነበር ያሉት ኃላፊዋ እነዚህ ግለሰቦች እስከ አምስት ዓመት እስርም እንደሚጠብቃቸው ተናግረዋል።












