በደቡብ አፍሪካ የሙስና ወንጀሎች መርማሪው ከልጃቸው ጋር ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ የሙስና ወንጀሎችን የሚመረምሩት ግለሰብ በተከፈተባቸው ተኩስ ከልጃቸው ጋር ተገደሉ።
ክሎቴ ሙሬይ የተባሉት የ50 ዓመቱ መርማሪ ቧሳሳ ከተባለው እና ከመንግሥት ጋር በገባቸው በርካታ የቅሌት ውሎች የሚታወቀውን ድርጅት መርምረዋል።
በተጫማሪም ምንም እንኳን ኩባንያው ክሱን ባይቀበልም ጉቦ በመስጠት የተጠረጠረ አንድ ትልቅ ኩባንያ ላይ ምርመራ አድርገዋል።
በሟቹ መርማሪ እና ሲመረምሯቸው በነበሩት ጉዳዮች መካከል ግንኙነት መኖሩን ወይም አለመኖሩን ፖሊስ ይመለከተዋል ተብሏል።
መርማሪው ባለፈው ቅዳሜ የሕግ አማካሪ ከሆነው የ28 ዓመት ልጃቸው ቶማስ ጋር መኪናቸውን እየሽከረከሩ ሳለ ማንነቱ ባልታወቀ ሰው ተተኩሶባቸው ተገድለዋል።
ልጃቸው ወዲያው እንደሞተ እና እሳቸው ግን ሆስፒታል ከገቡ በኋላ ሕይወታቸው ማለፉን የደቡብ አፍሪካ መገናኛ ብዙኃን የፖሊስ ቃል አቀባዩን ጠቅሰው ዘግበዋል።
አባት እና ልጅ ፕሪቶሪያ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው እያቀኑ ሳለ መገደላቸውን መገናኛ ብዙኃኑ ዘግበዋል።
ሙሬይ በፍርድ ቤት የተዘጉ ኩባንያዎችን እንዲመረምሩ፣ ንብረቶችን እንዲያስመልሱ እና ወንጀሎችን ሪፖርት እንዲያደርጉ ተሹመው ነበር።
ከእነዚህ ድርጅቶች መካከል አንዱ ቧሳሳ ነው። ቧሳሳ በተለይም በእስር ቤቶች አገልግሎት ላይ የተሰማራ ሲሆን ከመንግሥት ጋር ውል የሚገባ ነው።
ታዋቂው ዞንዶ የተባለው የፀረ ሙስና ኮሚሽን ቧሳሳ እንደ አውሮፓውያኑ ከ2009 እስከ 2018 በነበረው የጃኮብ ዙማ የሥልጣን ዘመን ለመንግሥት ባለሥልጣናትን እና ፖለቲከኞች ጉቦ ይሰጥ እንደነበር ደምድሟል።
ዙማ ለምርመራው አልተባበርም ቢሉም የሙስናውን ክስ አይቀበሉትም።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2018 የአሁኑ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ከቧሳሳ የተቀበሉትን 35 ሺህ ዶላር መልሰው እንደሚከፍሉ ገልጸዋል።
ራማፎሳ የገንዘብ ስጦታውን በተመለከተ ፓርላማውን እንዳሳሳቱት የፀረ ሙስና ኮሚሽኑ ቢደርስበትም ጉዳዩ በፍርድ ቤት ውድቅ ተደርጓል።
ራማፎሳ ባይቀበሉትም በሌላም ሙስና እንደተሳተፉ ተወርቶባቸዋል።
ሟቹ መርማሪ ጉፕታ ብራዘርስ የተባለው ድርጅትንም የሙስና ጉዳዮችን ሲመረምሩ ነበር።
ዞንዶ ኮሚሽን ኩባንያው በዙማ የሥልጣን ዘመን የመንግሥትን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ላይ ጫና ለማሳደር ሞክሯል ብሏል።
ጉፕታ ብራዘርስ እንደ አውሮፓውያኑ በ1993 ከሕንድ ወደ ደቡብ አፍሪካ የተዘዋወረ ሲሆን፣ ከመንግሥት ኩባንያዎች ጋር ከፍተኛ ትርፍ የሚያስገኙ ውሎችን በመፈረም የሚታወቅ ነው።
የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ የታሰሩት ጉፕታ ብራዘርስ ወደ ደቡብ ተዘዋውረው ለፍርድ እንዲቀርቡ እየሰሩ ነው።
ኩባንያው የመንግሥትን ውል ለማግኘት ጉቦ ይሰጣል መባሉን ግን አስተባብሏል።












