የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የቀጣይ ቀናት ጨዋታዎች ግምት

ታትሟል

በምንም ነገር ላይ እርግጠኛ መሆን አይቻልም ይባላል።

ማንቸስተር ዩናይትድስ በሊቨርፑል መሸነፉ እርግጥ ነው?

“ከአስሩ የሊጉ ጨዋታዎች ብቸኛው በእርግጠኝነት የምገምተው ጨዋታ ነው” ይላል የቢቢሲው ክሪስ ሱቶን።

“ማንቸስትር ስንት ጎል ያስተናግዳል? የሚለው ነው ጥያቄው። ከድጡ ወደ ማጡ እንደሚሆንባቸው እርግጠኛ ነኝ” ይላል።

ሱቶን ከሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ውጪም የሌሎችንም ጨዋታዎች ግምት አስቀምጧል።

ቅዳሜ

ቶተንሃም ከ ዎልቭስ

ባለፈው ሳምንት ቶተንሃም ከቼልሲ ጋር በነበረው ጨዋታ ባሳየው አቋም ተበሳጭቻለሁ።

ዎልቭሶች ፖርቹጋላዊውን ጎንካሎ ጉዋዴዝን በማስፈርም የፊት መስመራቸውን አጠናክረዋል።

ዎልቭሶች ባለፈው ዓመት የማጥቃት መስመራቸው ስስ መሆኑ ታይቷል።

ቶተንሃም ተመሳሳይ ችግር የለበትም።

ግምት፡ 3 - 1

ክሪስታል ፓላስ ከ አስቶን ቪላ

ክሪስታል ፓላስ ሰኞ ዕለት ከሊቨርፑል ጋር ድንቅ ፉክክር አድርጓል።

ከውጤቱም ጥሩ መነሳሳት ያገኛሉ ብዬ አስባለሁ።

ቪላም ከኤቨርተን ጋር ከነበረው ጨዋታ ጥሩ መነቃቃት ያገኛል ብዬ አስባለሁ።

ይህ ለመገመት ከባድ የሆነ ጨዋታ ነው።

ግምት፡ 1 - 1

ኤቨርተን ከ ኖቲንግሃም ፎረስት

ኖቲንግሃም ፎረስት ባለፈው ሳምንት ዌስት ሃምን በማሸነፍ ትልቅ ውጤት አስመዘግቧል።

ኤቨርተንም የውድድር ዓመቱን በጥሩ መልኩ ለማስኬድ ተመሳሳይ ድል ይፈልጋል።

ቡድኑ ይህ ነው የሚባል ጥሩ አጥቂ የለውም።

በዚህ ጨዋታ ግን ውጤቱ ይቀናቸዋል ብዬ እገምታለሁ።

ግምት፡ 2 - 0

ፉልሃም ከ ብሬንትፎርድ

የብሬንትፎርድ ጉዞ ተመችቶኛል። ባለፈው ሳምንት 3 ለ 0 ማንቸስተር ዩናይትድን ያሸንፋሉ ብዩ 4 ለ 0 አሸንፈዋል።

ፉልሃም ደግሞ ከሊቨርፑል ነጥብ በተጋራበት መንገድ ይጫወታል ብዬ አስባለሁ።

ከፍተኛ ፉክክር ያለው ጨዋታ ይሆናል።

ፉልሃም ሁለቱንም የመክፈቻ ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። የዚህ ሳምንቱም ተመሳሳይ ይሆናል።

ግምት፡ 1 - 1

ሌስተር ከ ሳውዝሃምፕተን

የሳውዝሃምፕተኑ አለቃ ራልፍ ሃሰንሃልት ጫና ውስጥ ወደቁ ይመስላል።

በቅድመ ውድድር ወቅት በሦስት ተከላካይ ቢጫወቱም ሊጉ ሲጀመር ወደ አራት ተከላካይ ተመልሰዋል።

ሌስተሮች በተከላካይ መስመር ላይ ክፍተት ቢኖርባቸውም ወደ ፊት ሲሄዱ ግን ጥሩ ናቸው።

በዚህ ጨዋታ ጎል የሚቆጠር ሲሆን የብሬንዳን ሮጀርስ ቡድን እንደሚያሸንፍ እገምታለሁ።

ግምት፡ 2 - 1

በርንማውዝ ከ አርሴናል

አርሴናል ድንቅ አጀማመር ያደረገ ሲሆን፣ ጋብርኤል ጂሰስም ልዩነት ፈጣሪ መሆን ችሏል።

ስለዝውውሩ ብዙ የተባለ ሲሆን እሱም ማስመከር ችሏል። በዚህ ጨዋታ ግን ጎል አያስቆጥርም።

በመድፈኞቹ አጀማመር ተደንቀን ለዋንጫ ልንገምታቸው ይገባል የሚል ግምት የለኝም።

በርንማውዝ ባለፈው ሳምንት በማንቸስትር ሲተቲ ተሸንፏል።

ግምት፡ 0 - 2

እሑድ

ሊድስ ከ ቼልሲ

ሊድስ ከሳውዛሃምፕተን ጋር በነበረው ጨዋታ ከ2 ለ 0 ከመምራት አቻ መለያየታቸው የሚያስቆጭ ነው።

የቼልሲ የፊት መስመር አሁንም ያልተመለሰ ጥያቄ አለበት።

ከቶትንሃም ጋር በነበረው ጨዋታ ግን ድንቅ ነበሩ።

ኤላንድ ሮድ ላይ በተተመሳሳይ መንገድ ከተጫወቱ ሦስት ነጥቡን ያሳካሉ።

ግምት፡ 0 - 3

ዌስት ሃም ከ ብራይተን

ዌስት ሃሞች የመጀመሪያዎቹን ሁለት ጨዋታዎች ቢሸነፉም በቅድመ ውድድር ዘመን ከደረሰባቸው የጉዳት መጠን አንጻር ስጋት ሊኖር አይገባም።

ውጤቱን በቅርቡ እንደሚያሻሽሉ ጥርጥር የለኝም።

ብራይተንን ባለፉት አስር ጨዋታዎች ማሸነፍ አለመቻላቸውን ግን አሁንም አይቀይሩትም።

የግረሃም ፖተር ቡድን በደንብ የተቀናጀ ሲሆን ነጥብ እንደሚያገኝም እገምታለሁ።

ግምት፡ 1 - 1

ኒውካስል ከ ማንቸስትር ሲቲ

በኒውካስል ሜዳ ድንቅ ድባብ እንደሚፈጠር እና አንድ ወይም ሁለት ዕድል እንደሚፈጥሩ አስባለሁ።

ጨዋታው በማንቸስተር ሲቲ የበላይነት እንደሚጠናቀቅ እገምታለሁ።

ኤርሊንግ ሃላንድ በበርንማውዝ ጨዋታ ተሳትፎው ዝቅ ያለ ነው ቢባልም ለኢካይ ጉዶዋን ጎል ማስቆጠር ዕድል አመቻችቷል።

ኒውካስሎች አጥቂውን ላይ በማተኮር ለመቆጣጠር ካሰቡ ለሌሎች ክፍተት ሊፈጥርላቸው ይችላል።

ግምት፡ 1 - 3

ሰኞ

ማንቸስተር ዩናይትድ ከ ሊቨርፑል

ማንቸስተሮች ይህንን ጨዋታ ካሸነፉ ከሊቨርፑል በላይ ይቀመጣሉ። ግን አይሳካላቸውም።

ኤሪክ ቴን ሃግ ያላቸውን ቡድን እንዴት እንደሚቀይሩ አላውቅም።

ሊቨርፑል ካደረገው ደካማ አጀማመር ሌላ የዳርዊን ኑኔዝ ቅጣት እና ጉዳቶች እንቅፋት ይሆኑባቸዋል።

ምንም ቢሆን ግን የየርገን ክሎፕ ቡድን የበላይነቱን ይይዛል።

ግምት፡ 1 - 5