በርካቶችን በስቅላት ሞት የቀጡት ባንግላዴሻዊ አረፉ

ታትሟል

በባንግላዴሽ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸውን በርካታ ሰዎችን በስቅላት የቀጡት እና ስለ ጉዳዩም መጽሃፍ የጻፉት ግለሰብ ህይወታቸው አለፈ።

ግለሰቡ የበርካታ ሰዎችን ህይወት የቀጠፉ እንዲሁም ፖለቲከኞችን በስቅላት ሞት ቀጥተዋል።

የ74 ዓመቱ ሻህጃሃን ቡይያን ሰኞ ዕለት ደረታቸው ላይ ህመም ከተሰማቸው በኋላ በዋና ከተማዋ ዳካ በሚገኝ ሆስፒታል ተወስደው ነበር።

በኋላም በህክምና ላይ እያሉ ህይወታቸው ማለፉን የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ግለሰቡ ቢያንስ 26 የሞት ቅጣቶችን ፈጽመዋል ተብሎ የሚታመን ሲሆን ነገር ግን አንዳንድ ዘገባዎች ቁጥሩን ወደ 60 ከፍ አድርገውታል።

የቀድሞው አብዮተኛ የነበሩት እኚህ ግለሰብ በስርቆት እና በግድያ ወንጀል የ42 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸው በእስር ላይ እያሉም ነው የስቅላት ሞት ፈጻሚ የሆኑት።

ሻህጃሃን የእስር ጊዜያቸው እንዲያጥር ነበር በስቅላት በሞት ቅጣትን ለመፈጸም በጎ ፈቃደኛ የሆኑት። በዚህም የተነሳ ከተፈረደባቸው አስር ዓመት ተቀንሶላቸው ባለፈው ዓመት ከእስር ተለቀዋል።

እሳቸው በስቅላት ሞት ከቀጧቸው መካከል የአገሪቱ መስራች እና የአሁኑ የባንግላዴሽ ጠቅላይ ሚኒስትር አባት የሆኑት ሼክ ሙጂቢር ራህማንን በመግደል የተፈረደባቸው ወታደራዊ መኮንኖች ይገኙበታል።

በጦር ወንጀል የተከሰሱትን ፖለቲከኞች አሊ አህሳን ሙጃሂድ እና ሳላሁዲን ኳደር ቻውዲሪ እንዲሁም በርካታ ሰዎችን በመግደል የሚታወቀውን ኤርሻድ ሽክደርን በሞት የቀጡት እኚሁ ሰው ናቸው።

ሻህጃሃን በስቅላት ሰዎችን የመቅጣት ሚናቸውን ሲከላከሉም ተደምጠዋል “እኔ ባልሰቅላቸው ሌላ ሰው ያደርገዋል” ሲሉ መናገራቸው በአንድ ወቅት ተዘግቧል።

ሰዎችን በስቅላት በመቅጣት ስላሳለፉት ህይወት እንዲሁም የስቅላት ሞት እንደሚፈጸም ማብራሪያዎችን ያካተተ መጽሓፍ አሳትመው ከፍተኛ ትኩረትን ስቧል።

ከእስር ከተለቀቁ በኋላ ከእሳቸው በ50 ዓመት የምታንስ ታዳጊ ልጅ ለአጭር ጊዜ አግብተው የነበረ ሲሆን በዚህም ምክንያት ህጋዊ ችግሮች አጋጥመዋቸው እንደነበር ዳካ ትሪቡን ዘግቧል።