ኤኳዶር ውስጥ በጥይት የተገደሉት ፖለቲከኛ ከንቲባ እንዲሆኑ ተመረጡ

የፎቶው ባለመብት, REVOLUCION CIUDADANA
በኢኳዶር ምርጫ ሲደረግ የድምጽ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ከመጀመሩ ከሰዓታት በፊት የተገደሉት ዕጩ ፖለቲከኛ ፖርቶ ሎፔዛ የተባለች ከተማ ከንቲባ ሆነው ተመረጡ።
ኦማር ሜኔዴዝ የተባሉት የ41 ዓመቱ ፖለቲከኛ ወደ መኖሪያ ቤታቸው በኃይል በገቡ ታጣቂዎች በጥይት ተመትተው የተገደሉት ባለፈው ቅዳሜ ነበር።
ከምርጫ ዘመቻ ሠራተኞቻቸው ጋር የነበሩት ፖለቲከኛው በጥቃቱ ሲገደሉ በተጨማሪ ሌላ በአፍላ በአስራዎቹ እድሜ የሚገኝ ሰውም መገደሉን ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል።
በኢኳዶር የከተማ አስተዳዳሪዎች ምርጫ የተካሄደው በአገሪቱ ከዕጽ አዘዋዋሪዎች ጋር የተያያዘ በተደራጁ አደገኛ ቡድኖች የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶች በተባረከቱበት ወቅት ነው።
በአገሪቱ በምርጫ ወቅት ዕጩ ፖለቲኞች ሲገደሉ ይህ የመጀሪያው አይደለም። ከሁለት ሳምንታት በፊት ሳሊናስ ለምትባል ከተማ ለከንቲባነት ሲወዳደሩ የነበሩ ፖለቲከኛ በጥይት ተመትተው ተገድለዋል።
ነገር ግን አስካሁን ከዚህ የግድያ ወንጀል ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር አውሎ ክስ የመሰረተበት ሰው የለም።
በተጨማሪም ለከንቲባነት ከተመረጡት ኦማር ሜኔዴዝ ግድያ ጋር በተያያዘም አስካሁን በቁጥጥር ሥር የዋለ የለም።
የዐይን እማኞች እንዳሉት በኦማር ሜንዴዝ ላይ ግድያውን የፈጸመው ግለሰብ በሞተር ብስክሌት አምልጧል።
በላቲን አሜሪካዋ አገር ኤኳዶር የተደራጀ ወንጀል መበራከት ያሳሰባቸው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጉሌርሞ ላሶ ግድያዎቹን አውግዘዋል።
ፕሬዝዳንቱ በአገሪቱ ሕገ-መንግሥት ላይ በርካታ ለውጦችን በማድረግ ዜጎች ድምጽ እንዲሰጡት አድርገዋል።
ከለውጦቹ መካከል በሌሎች አገራት በሕግ የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ መስጠትን ይጨምራል።
በቅርብ ዓመታት በአገሪቱ ወንጀል ድርጊቶች መበራከትን ተከትሎ እስር ቤቶች በታራሚዎች በመጨናነቃቸው እንደ አሜሪካ ባሉ አገራት የተፈረደባቸው የኢኳዶር ዜጎች የሆኑ ወንጀለኞችን አሳልፎ መስጠት ወጪ ቆጣቢ እና ከደኅንነት አንጻር የተሻለ አማራጭ ነው ብለው የሚከራከሩ ፖለቲከኞች አሉ።
የኢኳዶር ጎረቤት አገር ኮሎምቢያ እአአ 1997 በሕገ-መንግሥቷ ላይ ማሻሻያ ካደረገች በኋላ፣ አደገኛ ዕጽ አዘዋዋሪዎችን ለአሜሪካ አሳልፋ ስትሰጥ ቆይታለች።
ኢኳዶርም በተመሳሳይ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ሕዝበ ውሳኔ ብታደርግም ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያው የሕዝብ ተቀባይነት ሳያገኝ በድምጽ ሰጪዎች ውድቅ ተደርጓል።












