ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሁሉም በሚባል ደረጃ ከ80 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዋ በኮቪድ የተያዘባት የቻይና ግዛት
ሔናን ትባላለች። በቻይና ሦስተኛዋ ከፍተኛ ሕዝብ ጥቅጥቅ ብሎ የሚኖርባት አውራጃ ናት።
ከነዋሪዎቿ 88 ሚሊዮን የሚሆነው ሕዝብ በኮቪድ ተይዟል ተብሎ ይታመናል።
ይህም የጠቅላላ ነዋሪዋ 90 ከመቶ ሕዝብ ማለት ነው።
በጋዜጣዊ መግለጫቸው የግዛቲቱ የጤና ኃላፊ ካን ኹዋንቼንግ እንደተናገሩት 88.5 ሚሊዮን ሕዝብ ኮቪድ ይዞታል።
በቻይና ፍጹም ባልተጠበቀ ፍጥነት ተህዋሲው እንደ ሰደድ እሳት እየተዛመተ ነው።
ይህም የሆነው ቻይና ‘ዜሮ ኮቪድ ፖሊሲ’ የምትለው አቋሟን በቀየረች ቅጽበት ነው።
የሄናን የጤና ኃላፊ ይህ አሐዝ ከመቼ ጀምሮ የተመዘገበ እንደሆነ ባይገልጹም፣ ብዙዎች ግን የእንቅስቃሴ ገደቡ መነሳቱን ተከትሎ እንደሆነ ይጠረጥራሉ።
የሔናን አስደንጋጭ አሐዝ ግን የቻይና ማዕከላዊ መንግሥት እየሰጠ ካለው አሐዝ ጋር ፍጹም የሚጣረስ ነው።
ማዕከላዊው መንግሥት 1.4 ቢለዮን ሕዝቤ ውስጥ በኮቪድ የተያዘው 120ሺህ ብቻ ነው ይላል።
ዜሮ ኮቪድ ፖሊሲ ከተነሳ በኋላ የሞቱት ደግሞ 30 ሰዎች ናቸው ይላሉ የቻይና ባለሥልጣናት።
እሑድ ዕለት ለምሳሌ በመላው ቻይና ሦስት ዜጎች ብቻ ናቸው በኮቪድ ምክንያት የሞቱት ብሏል መንግሥት።
ቁጥሩ እንዲህ የቀነሰው የቻይና መንግሥት ኮቪድ ተህዋሲ ባስከተለው የጤና መወሳሰብ የሚሞቱ ሰዎች በኮቪድ ሞቱ ተብሎ ሪፖርት እንዳይደረግ መመሪያ ካስተላለፈ በኋላ ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት ቻይና በኮቪድ የሚሞቱባት ዜጎቿን አሐዝ እየቀነሰች መሆኑ አሳስቦኛል ሲል የገለጸው ባለፈው ሳምንት ነበር።
አንዳንድ የአገሪቱ ግዛቶች ግን ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር የማይስማማ አሐዝ እያወጡ ይገኛሉ።
ለምሳሌ የወደብ ከተማ የሀነችው ኪንግዳዎ ከተማ አንድ የጤና ኃላፊ በፈረንጆች ገና ዋዜማ በሰጡት ማብራሪያ በከተማዋ ግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ በየቀኑ በኮቪድ ይያዛል ብለው ነበር።
ይህ ዜና ግን ቶሎ ከድረ ገጽ እንዲነሳ ተደርጓል።
ከእሑድ ጀምሮ ቤይጂንግ በተጓዦች ላይ ጥላው የነበረውን እገዳ አንስታለች።
ከትናንት ሰኞ ጀምሮ ደግሞ ድንበሮቿን ለጎብኚዎች ክፍት አድርጋለች።
አንድ የእንግሊዝ የጤና መረጃዎችን የሚያጠናቅር ኩባንያ በቻይና በየቀኑ 14ሺህ ሰዎች በኮቪድ እየሞቱ ነው ብሏል።
የቻይና አዲስ ዓመትን ተከትሎ 2 ቢሊዮን ጉዞዎች ይደረጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይህን ከፍተኛ የሕዝብ እንቅስቃሴ ተከትሎ ምናልባት ተህዋሲው ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሊዛመት ይችላል የሚል ስጋት አለ።
አሜሪካ፣ ካናዳ እና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በርካታ አገራት ከወዲሁ ከቻይና ለሚመጡ ተጓዦች የኮቪድ ነጻ ሰርተፍኬት እየጠየቁ ነው።