ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የስድስት ዓመቱ ታዳጊ አስተማሪውን ያቆሰለው በእናቱ ሕጋዊ ሽጉጥ መሆኑን ፖሊስ ገለጸ
በአሜሪካ ትምህርት ቤት ውስጥ አስተማሪውን ተኩሶ ክፉኛ ያቆሰለው የስድስት ዓመት ታዳጊ እናቱ በሕጋዊ መንገድ የገዛችውን ሽጉጥ መጠቀሙን ፖሊስ አስታወቀ።
ፖሊስ ባለፈው ሳምንት አርብ በቨርጂኒያ ግዘት ውስጥ በሚገኝ ትምህርት ቤት የተከሰተውን ሁኔታ በተመለከተ በሰጠው መግለጫ ላይ የስድስት ዓመቱ ታዳጊ ተማሪ የእናቱን ሽጉጥ በጀርባው በሚያዝለው ቦርሳው ውስጥ ይዞ ትምህርት ቤት መምጣቱን ገልጿል።
ታዳጊው በመምህሩ በሆነችው አቢጌል ዚወርነርን ሆን ብሎ ተኩሶ ያቆሰላት ክፍል ውስጥ መሆኑን ፖሊስ አመልክቶ፣ መምህርቷ በጥይት ከተመታች በኋላ ሌሎች ተማሪዎቿ እንዳይጎዱ ከክፍል በማስወጣት እርዳታ ጠርታለች።
የ25 ዓመቷ ወጣት መምህርት ዚወርነር አሁንም ሆስፒታል ውስጥ ስትሆን በደህና ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ ፖሊስ ገልጿል።
ክስተቱ ያጋጠመው ከስድስት አስከ ሰባት ዓመት የሚሆኑ ተማሪዎች በሚገኙበት አንደኛ ክፍል ውስጥ ሲሆን፣ በመምህርቷ እና በታዳጊው መካከል ጭቅጭቅ ከተፈጠረ በኋላ ነው ጥይት የተተኮሰው።
ፖሊስ መምህርቷን “ጀግኒት” ያላት ሲሆን፣ ሆስፒታል ውስጥም ሆና እሷ በጥይት በተመታችበት ጊዜ ክፍል ውስጥ የነበሩት ሁሉም ተማሪዎቿ ደህና ስለመሆናቸው ደጋግማ እንደምትጠይቅ ገልጿል።
የስድስት ዓመቱ ታዳጊ ባለፈው ዐርብ መምህሩን ተኩሶ በጥይት ከመታት በኋላ ቨርጂኒያ ውስጥ ከሚገኘው ሪችኔክ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጥሪ እንደደረሰው የገለጸው ፖሊስ፣ በስፍራው ሲደርሱም ታዳጊው በትምህርት ቤቱ ሠራተኞች ተይዞ አግኝተውታል።
180 ሺህ ያህል ነዋሪ ያለባት የኒውፖርት ኒውስ ከተማ የፖሊስ አዛዡ ስቲቭ ድሪው እንደተረናገሩት ተማሪው በመምህርቷ ላይ አንድ ጥይት ብቻ ነው የተኮሰው።
ጨምረውም መምህርቷ እያስተማረች በነበረችበት ጊዜ የተተኮሰው ጥይት በድንገት ሳይሆን “ሆን ተብሎ የተተኮሰ ነው” ብለዋል።
መምህርቷ በጥይቱ በክንዷ በኩል ደረቷን የመታት ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ ሌሎች ተማሪዎቿ እንዳይጎዱ ከክፍሉ በማስወጣት ወደ ትምህርት ቤቱ አስተዳደር ቢሮ ሄዳ እርዳታ ለማግኘት ሞክራለች።
አንድ ወላጅ ለዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ እንደተረናገሩት ጥይቱ የተተኮሰው መምህርቷ ከታዳጊው የያዘውን ሽጉጥ ለመንጠቅ በሞከረችበት ጊዜ ነው።
ፖሊስ እንዳለው ክስተቱ ባጋጠመበት ክፍል ውስጥ ታዳጊው ተማሪ በሚቀመጠብት ጠረጴዛ አቅራቢያ ሽጉጥ፣ በጀርባ የሚታዘል ቦርሳ፣ ሞባይል እና የተተኮሰ የጥይት ቀለህ አግኝቷል።
የፖሊስ አዛዡ እንደተናገሩት አስተማሪውን ያቆሰለው ተማሪ ሽጉጡ በሕጋዊ መንገድ ተገዝቶ ቤት ውስጥ ተቀምጦ የነበረ ነው። ይህንንም እናት በሰጠችው ቃል መሠረት ፖሊስ ማረጋገጥ ችሏል።
ጥቃቱን የፈጸመው ታዳጊ ማንነት ያልተገለጸ ሲሆን፣ ጥበቃ ወደ ሚደረግለት ቦታ ተወስዶ ሆስፒታል ውስጥ ምርመራ እየተደረገለት ነው።
ፖሊስ በጉዳዩ ዙሪያ ምርመራውን የቀጠለ ሲሆን፣ ለጊዜው በጥበቃ ሥር እንዲቆይ ከፍርድ ቤት ፈቃድ እንደሚጠይቅ አሳውቋል።
ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት 550 ያህል ተማሪዎች ያሉት ትምህርት ቤት መግቢያው ላይ ዘመናዊ የመፈተሻ መሳሪያ ያለው ሲሆን፣ በሁሉም ላይ ሳይሆን በተመረጡ ተማሪዎች ላይ ድንገተኛ ፍተሻ ይደረግበት ነበር።
መምህርቷን ያቆሰለው ተኩስ ከተከሰተ በኋላ በትምህርት ቤቱ ውስጥ የነበሩት ተማሪዎች በሙሉ በስፖርት አዳራሽ ውስጥ ሆነው ወላጆቻቸውን እንዲጠብቅ ተደርጓል።
በስፍራውም የደነገጡና የሚያለቅሱ ወላጆች ልጆቻቸውን ለመውሰድ ሲጠባበቁ እንደነበረ ፖሊስ ገልጿል።
የተከሰተውን ሁኔታ ተከትሎ ከተፈጠረው ድንጋጤ ወላጆች እና ተማሪዎች እንዲያገግሙ ትምህርት ቤቱ በዚህ ሳምንት ዝግ ሆኖ ይቆያል።
በቨርጂኒያ ግዛት ውስጥ የምትገኘው የኒውፖርት ኒውስ ከተማ 180,000 የሚደርስ ነዋሪ ያላት ስትሆን፣ ከግዛቲቱ ዋና ከተማ ሪችመንድ በስተደቡብ 112 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።