ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በብራዚል ነውጥ የሚወነጀሉት ፕሬዝዳንት ዣየር ቦልሶናሮ ሆስፒታል ገቡ
ብራዚል ውስጥ በተከሰተው አመጽ ውስጥ እጃቸው ሳይኖር አይቀርም የተባሉት የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዣየር ቦልሶናሮ ሆስፒታል ገቡ።
ባለቤታቸው ሚሸል ቦልሶናሮ እንደተናገሩት ዣየር ቦልሶናሮ በአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት፣ ኦርላንዶ አቅራቢያ ወደ ሚገኝ ሆስፒታል የገቡት የሆድ ሕመም ገጥሟቸው ነው።
ቦልሶናሮ በ2018 በስለት የመወጋት አደጋ ካጋጠማቸው ወዲህ አልፎ አልፎ ሆዳቸው አካባቢ ሕመም ያጋጥማቸዋል።
'የትሮፒካሉ ትራምፕ' በሚል ቅጽል ስም የሚጠሩት አክራሪው ብሔርተኛ ቦልሶናሮ፣ ብራዚል ውስጥ እሑድ በተቀሰቀሰው ከባድ ነውጥ እጃቸው እንዳለበት ሲነገር ነበር።
በፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ በጠባብ ውጤት በምርጫ ከተሸነፉ በኋላ ቦልሶናሮ ውጤቱን ውድቅ አድርገው የአመጽ ጥሪ ያደርጋሉ የሚል ከፍተኛ ፍርሃት ነበር።
ይሁንና ቦልሶናሮ በአዲሱ ፕሬዝዳንት በዓለ ሲመት ላለመገኘት ከመርሐ ግብሩ ጥቂት ሰዓት ቀደም ብለው ብራዚልን ለቀው በአሜሪካ ደቡባዊ ግዛት ፍሎሪዳ ኑሮ ጀምረዋል።
ቦልሶናሮ እንደ አሜሪካኑ ዶናልድ ትራምፕ ሁሉ ነውጠኛ ደጋፊዎች ያሏቸው ሲሆን ባለፈው እሑድ ደጋፊዎቻቸው አደባባይ በመውጣት ፓርላማውን ሰብረው በመግባት ከፍተኛ ውድመት አድርሰዋል።
በተመሳሳይ በከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ሕንጻ ላይ ብዙ ጥፋት ከፈጸሙ በኋላ ቤተ መንግሥቱ ላይ ከበባ ፈጽመዋል።
ይህ ድርጊታቸው ከሁለት ዓመት በፊት ዶናልድ ትራምፕ በጆ ባይደን ከተሸነፉ በኋላ የትራምፕ ደጋፊዎች በጃንዋሪ 6/2020 የፈጸሙትን የካፒቶል ሒል አመጽ የሚመስል ነው።
የትራምፕ ደጋፊዎች ለብራዚል አቻዎቻቸው “ግፉበት ከጎናችሁ ነን” እያሉ ‘ትሩዝ ሶሻል’ በተሰኘው የትራምፕ ማኅበራዊ ሚዲያ ሲያበረታቱ ነበር።
ከዚህም ሌላ የትራምፕ የአመጽ አማካሪ ናቸው የሚባሉት ስቲቭ ባነን ከቦልሶናሮ የበኩር ልጅ ጋር ቀደም ብለው መገናኘታቸው ምናልባት ከአመጹ ጀርባ የዶናልድ ትራምፕ ሰዎች አሉበት ተብሎ እንዲጠረጠር አስችሏል።
ጆ ባይደን ከአንዳንድ የፓርቲያቸው ሰዎች ቦልሶናሮን ከአሜሪካ እንዲያስወጧቸው ጫና በርትቶባቸዋል።
አንድ የዲሞክራቲክ ፓርቲ እንደራሴ ለሲኤንኤን ሲናገሩ “ቦልሶናሮ ከፍሎሪዳ መውጣት አለበት፤ አሜሪካ የአምባገነኖች መጦርያ መሆን የለባትም” ብለዋል።
አሌክሳንድሪያ ኦካሺዮ ኮርቴዝ የተባሉ ሌላ ዲሞክራት የኮንግረስ አባል አሜሪካ ለቦልሶናሮ ጥገኝነት መስጠት “ትርጉሙ አይገባኝም” ብለዋል።
ነገር ግን ለጊዜው የብራዚል መንግሥት በይፋ ቦልሶናሮ ተላልፈው እንዲሰጡት አልጠየቀም።
ፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ እሑድ ነውጥ ላይ የተሳተፉት በሙሉ የእጃቸውን ያገኛሉ ሲሉ ዝተዋል።
ይህን ተከትሎም ከአንድ ሺህ አምስት መቶ ሰዎች የሚበልጡ ተጠርጣሪዎች ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሏል።
ቦልሶናሮ በምርጫ ተሸንፊያለሁ ብለው በይፋ ለሉላ ዳ ሲልቫ መልካም ምኞት ሳይመኙላቸው ነው ወደ አሜሪካ ያቀኑት።
የእሑዱን አመጽ በተመለከተም “ድርጊቱ ትክክል አይደለም” ብለው ለማውገዝ ቦልሶናሮ ስድስት ሰዓታትን ወስዶባቸዋል።
የእሑዱን አመጽ በመቃወም በአስር ሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ ዛሬ በሳዎ ፖሎ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ እያደረገ ነው።
ሉላ ዳ ሲልቫ ግራ ዘመም ሲሆኑ ቦልሶናሮ ቀኝ አክራሪ ብሔርተኛ ናቸው።
ሉላ ከዚህ ቀደም አገሪቱን ወደላቀ የኢኮኖሚ ደረጃ እንዳደረሱ ይነገርላቸዋል።
ሆኖም በ2017 በሙስና ተጠርጥረው 9 ዓመት እስር ከተፈረደባቸው በኋላ 18 ወራትን ማረሚያ ቤት አሳልፈው ፍርዱ ተቀልብሶ ነጻ ተብለዋል።
ከዚያ በኋላ ነው በድጋሚ ወደ ሥልጣን የመጡት።
215 ሚሊዮን የሚገመተው የብራዚል ሕዝብ በአሁኑ ሰዓት በፖለቲካ አቋም ለሁለት ተከፍሏል።
አሜሪካ፣ ካናዳ እና የአውሮፓ ኅብረት እሑድ የቦልሶናሮ ደጋፊዎች መንግሥት ለመገልበት ያደረጉትን ሙከራ ክፉኛ አውግዘዋል።