በፕሬዝዳንት ባይደን መኖሪያ ቤት መኪና ማቆሚያ ውስጥ ተጨማሪ ምስጢራዊ ሰነድ ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በፕሬዝዳት ጆ ባይደን የቀድሞ ቢሮ ውስጥ "ጥብቅ አገራዊ ምሥጢራዊ ሰነዶች" ከተገኙ በኋላ የፕሬዝዳንቱ ጎብኝዎችን ዝርዝር የያዘው መዝገብ እየተመረመረ ነው።
ሪፐብሊካኑ የምክር ቤት አባላት በባይደን መኖሪያ ቤቶች በአንዱ የተገኘው ሰነድ "ብሔራዊ የደኅንነት አደጋ" ነው ሲሉ የጎብኝዎች ስምና ማንነት የሚሰፍርበትን መዝገብ ለማየት እየጠየቁ ነው።
ሐሙስ ዕለት ደግሞ ፕሬዝዳንት ባይደን በዴልዌር በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው መኪና ማቆሚያ ውስጥ ምስጢራዊ ሰነዶች መገኘታቸውን ተናግረዋል።
በአሜሪካ ሕግ ‘ጥብቅ የአገር ምስጢር’ የተደረጉ ሰነዶች መቀመጥ የሚችሉት በፌዴራል ቤተ-መዘክር ውስጥ ብቻ ነው።
የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ ፋይሎቹን የሚያጣራ መርማሪ ሾሟል።
ባይደን ምክትል ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት የተጻፉ ጥብቅ አገራዊ ምስጥራዊ ሰነዶች በዋሽንግተን በሚገኘው በፔን ባይደን ሴንተር የመገኘታቸው ዜና የተሰማው በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ በባይደን መኖሪያ ቤት ሁለተኛው ሰነድ መገኘቱ ተገልጿል።
የመጀመሪያው ሰነድ ከአሜሪካ አጋማሽ ምርጫ በፊት በአውሮፓውያኑ ኅዳር 2 የተገኘ ሲሆን ወደ ሕዝብ የደረሰው ግን እጅግ ዘግይቶ ሰኞ ዕለት ነው።
ባይደን እንደ አውሮፓውያኑ 2017 ዋይት ሃውስን ለቀው ከወጡ በኋላ በ2019 የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዘመቻ እስከጀመሩበት ጊዜ ድረስ ቢሮውን እንደ መሰብሰቢያ አድርገው ይጠቀሙበት ነበር።
ሐሙስ ዕለት የአሜሪካ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሜሪክ ጋርላንድ፣ ሁለተኛው ሰነድ በደልዌር፣ ዊልሚንግተን በሚገኘው የባይደን የግል መኖሪያ ቤት ታኅሳስ 20 መገኘቱን ይፋ አድርገዋል።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ጨምረውም የባይደን ጠበቆች በዚያው የፕሬዝዳንቱ መኖሪያ ቤት ተጨማሪ ሰነዶች መገኘታቸውን ለማሳወቅ ሐሙስ ዕለት ጠዋት መርማሪዎችን ጠርተው እንደነበር ተናግረዋል።
በመሆኑን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ በትራምፕ አስተዳደር ጊዜ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩትን ሮበርት ሀር “አስገራሚ ሁኔታዎች" ባሉት የባይደን ሰነዶች ላይ የሚካሄደውን ምርመራ እንዲመሩ ሾመዋቸዋል።
አዲስ የተመረጡት ሪፐብሊካኑ የምክር ቤት አፈጉባኤ ኬቪን ማክ ካርቲ፣ ሰነዶቹ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የወጡበትን ጊዜ እጅግ የዘገየ መሆኑን በመጥቀስ ባይደን ሚስጢራዊ ሰነዶችን ሆነ ብለው በተገቢው መንገድ አልያዙም ሲሉ ከሰዋቸዋል።
የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ቴሌቪዥን በደረሰ ሌላ መረጃ ቀደም ብሎ የተገኙት ጥብቅ ምሥጢራዊ ሰነዶች በውስጣቸው የኒክሊየር ምሥጢርን የያዙ አይደሉም።
መሰል ምስጢራዊ ሰነዶች በፕሬዚደንት መኖሪያ ቤት ሲገኝ ይህ የመጀመሪያ አይደለም።
በተመሳሳይ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንዲህ ያሉ “ጥብቅ የአገር ምሥጢር” ተብለው ማኅተም ያረፈባቸው ሰነዶች በመኖሪያ ቤታቸው ተገኝተዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከሥልጣን ሲወርዱ እነዚህን ሰነዶች ወደ ፌዴራል ቤተ መዘክር መመለስ ሲኖርባቸው እርሳቸው ግን ወደ ቤታቸው ይዘው በመሄዳቸው ጉዳያቸው በልዩ ፍርድ ቤት እየተመረመረ ነው።












