የታዋቂው ናይጄሪያዊ ሙዚቀኛ ዴቪዶ ልጅ ሰምጦ መሞቱን ተከትሎ ፖሊስ በቤት ሰራተኞቹ ላይ ምርመራ ከፈተ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በአፍሮቢትስ ሙዚቃ ዘርፍ ስመ ጥር የሆነው የናይጄሪያው ሙዚቀኛ ዴቪዶ የሶስት ዓመት ልጁ ሰምጦ መሞቱን ተከትሎ ፖሊስ ስምንት የሚሆኑ የቤት ሰራተኞችን ለምርመራ ወስዷል።
የፖሊስ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንዳረጋገጠው ባሳለፍነው ወር ሶስት አመት የሞላው ህጻን ኢፌአኒ አዴለ ሰኞ እለት ሰምጦ መሞቱን ገልጸዋል።
ህጻኑ ሌጎስ በሚገኘው ወላጆቹ ቤት መዋኛ ገንዳ ውስጥ መስመጡንም የኃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ሙዚቀኛው እና ታዋቂዋ ሼፍ የሆነችው እጮኛው ቺዮማ ሮውላንድ በልጃቸው ሞት ላይ እስካሁን የሰጡት አስተያየት የለም።
ህፃኑ ሰምጦ የመሞቱ ዜና በአለም አቀፍ መዝናኛ ኢንዱስትሪ ውስጥ በሰፊው የተጋራ ሲሆን በርካታ አርቲስቶችም ለጥንዶቹ ኃዘናቸውን ገልጸዋል።
የፖሊስ ቃል አቀባይ ቤንጃሚን ሁንዴይን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከቤት ሰራተኞቸቻው መካከል አንደኛው ሰኞ እለት በአገሬው ሰአት አቆጣጠር 4 ሰዓት ከምሽቱ ስልክ መደወላቸውን ነው።
ቃለ አቀባዩ አክለውም ስምንት የቤት ሰራተኞች የፖሊስ ጥያቄን እንዲመልሱ መጠራታቸውንና ምርመራ መከፈቱንም አረጋግጠዋል።
“ስለ ህጻኑ አሟሟት ሁኔታ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የሲሲቲቪ ካሜራዎችን እየተመለከትን ነው” ብለዋል ቤንጃሚን
አክለውም “አስከሬኑ በሬሳ ክፍል ውስጥ ተቀምጧል። ከወላጆቹም ጋር ተገናኝተናል። ትናንት ማታ ፖሊስ ጣቢያ ነበሩ” ብለዋል።
ዴቪድ አዴሌክ ወይም በቅጽል ስሙ ዴቪዶ አፍሪካ ካፈራቻቸው ስመ ጥር ሙዚቀኞች አንዱ እንደሆነ ይታመናል።
በአለም ላይ ስመ ጥር የሆኑትን ኤምቲቪ እና ቢኢቲ የሙዚቃ ሽልማቶች አሸንፏል። ከታዋቂዎቹ ሙዚቀኞች ክሪስ ብራውን እና ኒኪ ሚናጅን ጨምሮ ከሌሎች አርቲስቶች ጋር ሙዚቃ ሰርቷል።
ባለፈው ወር ወደ ለንደን ባደረጉት ጉዞ ሙዚቀኛው ከእጮኛው ቺዮማ ሮውላንድ በሚቀጥለው ዓመት እንደሚጋቡ አስታውቀዋል።
ዘፋኙ ከሌሎች አጋሮች ጋር ሌሎች ሦስት ልጆች አሉት።
በአውሮፓውያኑ 2018 የናይጄሪያዊው ዘፋኝ ዲባንጂ የአንድ ዓመት ልጅም በተመሳሳይ ሁኔታ በመዋኛ ገንዳ ውስጥ ሰምጧል።












