ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩናይትድ በባከኑ ደቂቃዎች በተቆጠሩበት ጎሎች ውድ ሦስት ነጥቦችን አሳልፎ ሰጠ
ከሁለት ለባዶ ከመመራት ተነስቶ ቼልሲን 3 ለ 2 ሲመራ የነበረው ማንቸስተር ዩናይትድ በባከኑ ደቂቃዎች በተቆጠሩበት ጎሎች ተሸነፈ።
የቼልሲው ኮል ፓልመር ሃትሪክ በሰራበት ጨዋታ በባከኑ ደቂቃዎች ሁለት ጎሎችን አስቆጥሮ ቡድኑን አስደናቂ ድል አጎናጽፏል።
ፓልመር የቼልሲን የማሸነፊዋን ጎል 100 ደቂቃ 39 ሰከንድ ሲል ከማስቆጠሩ በፊት ዩናይትድ 99 ደቂቃ ከ17 ሰከንድ ላይ ጨዋታውን 3 ለ 2 እየመራ ነበር።
ይሁን እንጂ ባለሜዳዎቹ ቼልሲዎች በ90+10 እንዲሁም በ90+11 ላይ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ሦስት ነጥቡን ከቀያይ ሴጣኖቹ ነጥቀዋል።
የዩናይትድ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ከጨዋታው በኋላ “ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ይገባን ነበር። ሁለቱ ጎሎች ቀድመው ከተቆጠሩብን በኋላ የበላይነት በመያዝ ጥሩ ነበርን” ብለዋል።
በፕሪሚየር ሊጉ ትናንት ምሽት በተካሄደው ጨዋታ ቀዳሚውን ጎል ያስቆጠሩት ሰማያዊዎቹ ቼልሲዎች ነበሩ።
አምበሉ ኮነር ጋላጋር የመጀመሪያውን ጎል ሲያስቆጥር ፖል ፓልማር ደግሞ የዩናይትዱ አንቶኒ በቼልሲው ተከላካይ ማርክ ኩኩሪያል ላይ የፈጸመውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ፍጹም ቅጣት ምት ወደ ጎል ቀይሯል።
ቼልሲ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ሁለት ለዜሮ መምራት ቢጀምርም ዩናይትድ በአሌሃንድሮ ጋርናቾ ያገኛትን እድል ተጠቅሞ ጎል ማስቆጠሩ ወደ ጨዋታው እንዲመለስ አድርጎታል።
ከእረፍት በፊትም ዲያጎ ዳሎት ያሻማውን ኳስ አምበሉ ብሩኖ ፈርናንዴዝ ወደ በጭንቅላት ወደ ግብ ቀይሯት ጨዋታ 2ለ2 በሆነ ውጤት የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ 67ኛው ደቂቃ ላይ አንቶኒ ግሩም አድርጎ ለጋርናቾ ያቀበላት ኳስ በወጣቱ የክንፍ ተጫዋች ወደ ጎል ተቀይራ ዩናይትድ 2ለ0 ከመመራት ተነስቶ 3ለ2 መምራት ጀመረ።
ይህ ውጤትም እስከ 90+10 ድረስ ሄዷል።
በቀጣይ የውድድር ዓመት የቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊነቱን ለማረጋገጥ እየታገለ ያለው ዩናይትድ ከሜዳው ውጪ ቼልሲን አሸንፎ ውድ ሦስት ነጥቦችን ያገኘ መስሎ ነበር።
ይሁን እንጂ ባልተጠበቀ ሁኔታ ሰማያዊዎቹ ሁለት ጎሎችን አስቆጥረው ድሉን የራሳቸው አድርገዋል።
ዳሎት በቼልሲው ማዱዬኬ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ፍጹም ቅጣት ምት ኮል ፓልመር በ100ኛ ደቂቃ ወደ ግብ ሲቀይር ሁለቱ ክለቦች ነጥብ ተጋርተው የሚወጡም ምስሎ መስሎ ነበር።
ፖልመር 101 ደቂቃ ሲል ከማዕዘን ምት የተገኘችውን ኳስ አክሮሮ የመታት ኳስ የዩናይትድ ተጫዋችን ገጭታ ከመረብ ስትገናኝ ስታንፎርድ ብሪጅ በጮኀት ተናግቷል።
በዚህ ጨዋታ ልዩነት ፈጣሪ ሆኖ ያመሸው ኮል ፓርልመር፤ “በጣም አስገራሚ ነው። በእብደት የተሞላ። በጣም ደስተኛ ነኝ” ብሏል።
ፓልመር ትናንት ያስቆጠራቸው ሦስት ጎሎች በሊጉ ያገባቸውን ጎሎች ወደ 16 ከፍ አድርገውታል። ከሲቲው ሃላንድ በመቀጠልም ብዙ ጎል ያስቆጠረ ተጫዋችም ሆኗል።