የእስራኤል የፀጥታ ኃይሎች በዌስት ባንክ ሦስት ፍልስጤማዊያንን ገደሉ

ፍልስጤማዊያን ጄኒን አካባቢ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ፍልስጤማዊያን የእስራኤል ወታደሮች ሶስት ሰዎች በገደሉት ጄኒን አካባቢ ተሰባስበው ነበር
ታትሟል

የእስራኤል የፀጥታ ኃይሎች የፍልስጤም ሚሊሻ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሦስት ፍልስጤማዊያንን መግደላቸውን አስታወቁ።

ይህ የሆነው በቁጥጥር ሥር ባለችው ዌስት ባንክ ሲሆን ሥፍራው ጄኒን ለተባለው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ቀረብ ይላል።

ይህ መጠለያ ጣቢያ ባለፈው ወር እስራኤል በፈፀመችው የጦር እርምጃ ምክንያት መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

የአሁኑ ጥቃትም ሌላ ከፍተኛ አመፅ በሥፍራው እንዳይቀስቅስ ተሰግቷል።

አርብ ዕለት የታጠቁ የአይሁድ ሠፋሪዎች አንድ የፍልስጤማዊያን መንደርን አጥቅተው ታዳጊ ፍልስጤማዊ ሲገደል በሌላ በኩል አንድ የእስራኤል ፀጥታ ኃይል ቴል አቪቭ በተፈፀመ ጥቃት ተገድሏል።

የእስራኤል ጦር ባወጣው መግለጫ ቡድኑ ጥቃት ሊያደርስ ነበር፤ መኪናቸው ውስጥ አውቶማቲክ የጦር መሣሪዎች ተገኝተዋል ብሏል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ የፀጥታ ኃይላቸው የወሰደውን እርምጃ አድንቀዋል።

“እርምጃ መውሰድ እንቀጥላለን። በሁሉም ቦታ፤ በየትኛውም ጊዜ፤ እኛ ሊያጠቁ በሚነሱ ላይ እርምጃ እንወስዳለን” ብለዋል።

ሦስቱ ሰዎች የተገደሉት አንድ ፍልስጤማዊ የእስራኤል ፀጥታ ኃይል የሆነ ግለሰብን ቴል-አቪቭ ውስጥ በጥይት ከገደለው በኋላ ነው።

ፍልስጤማዊው ጥቃቱን ከፈፀመ በኋላ በአንድ ሌላ የፀጥታ ኃይል ተገድሏል።

እሑድ ዕለት ሦስቱ ፍልስጤማዊያን ከተገደሉ በኋላ የፍልስጤሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሐመድ ሽታየህ፤ “በጄኒን የተፈፀመው ወንጀል ሰዎች ከቅጣት መዳን እንደሚችሉ ቢያምኑ ኖሮ አይፈጠርም ነበር” ብለዋል።

የፍልስጤም ታጣቂ ቡድኖች ግድያውን አውግዘው በቀል ከመወሰድ እንደማይመለሱ ዝተዋል።

“ጠላት ከፍልስጤም ሕዝብ መሐል ሦስት ሰዎችን ገድሏል። ለፈፀመው ወንጀል ክፍያ ሳይፈፅም በሰላም አይኖራትም” ሲሉ የጋዛ መሪ የሆነው ሐማስ ቃል-አቀባይ ተናግረዋል።

ኢስላሚክ ጂሐድ የተሰኘው በጋዛና ዌስት ባንክ አባላት ያሉት ቡድን “ጠላት ለፈፀመው የክፋትና የሽብር ጥቃት ከባድ ምላሽ ይጠብቀዋል” ብሏል።

ባለፈው አርብ ወግ አጥባቂ የሆኑ የአይሁድ ሠፋሪዎች ዌስት ባንክ ወደ ሚገኝ የፍልስጤማዊያን መንደር ሄደው አንድ የ19 ዓመት ወጣት ከገደሉ በኋላ የእስራኤል ፖሊስ ጥቃቱን የፈፀሙት ሰዎች ታስረዋል ብሏል።

ዩናይትድ ስቴትስ ሰፋሪዎች የፈፀሙትን ጥቃት የሽብር ጥቃት ስትል ኮንናዋለች።

አሜሪካ መሰል ጠንካራ ቃል በመጠቀም ጉዳዩን መኮነኗ ከእስራኤል ቀኝ-ዘመም መንግሥት ጋር ያላት ግንኙነት መሻከሩን ያሳያል ተብሏል።

ጄኒን መጠለያ ጣቢያ ከእአአ 1950ዎቹ ጀመሮ በ1989-49 በተካሄደው የአረብ-እስራኤል ጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያንን ሲያስጠልል ቆይቷል።

የተባበሩት መንግሥታት ጄኒን በግምት 14ሺህ ሰዎችን አስጠልሎ ይዟል ይላል።