የዓለማችን ግዙፉ የዕፅዋት ዝርያ አውስትራሊያ ውስጥ ተገኘ

ታትሟል

በምድራችን ሰፊ ስፍራን በመያዝ ተወዳዳሪ የለውም የተባለለት የዕፅዋት ተክል አውስትራሊያ ውስጥ ተገኘ።

ይህ የውቅያኖስ ውስጥ ሣር ማንሃታን ከተሰኘችው የኒው ዮርክ አካል ሦስት እጥፍ የሚያክል መሬት ይሸፍናል።

ሳይንቲስቶች የዘረ መል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከውሃ በታች ተንሰራፍቶ የሚገኘው የዕፅዋት ዝርያ እንደሆነ ደርሰውበታል።

ይህ ከውሃ በታች የሚበቅል ሣር ዕድሜው 4500 ዓመት ሊሆን እንደሚችል ሳይንቲስቶች ይገምታሉ።

የሣር ዝርያው 200 ስኩዌር ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍን የዌስተርን አውስትራሊያ ዩኒቨርሲቲ አጥኚዎች ይገልጻሉ።

የአጥኚዎች ቡድኑ ይህን ዕፀዋት ያገኘው ፐርዝ ከተሰኘው የአውስትራሊያ ከተማ 800 ኪሎ ሜትር ራቅ ብሎ በሚገኘው ሻርክ ቤይ ሆነው ሳለ ነው።

በተለምዶ ሪበን ዊድ የሚባለው ሣር በአውስትራሊያ የውሃ ዳርቻ ከተማዎች በብዛት ይገኛል።

አጥኚዎቹ 18 ሺህ የዘረ መል መለያ መሣሪያዎችን ዘርግተው ከእያንዳንዱ ቅንጣት መረጃ ሰብስበዋል።

ሳይንቲስቶቹ ሐሳባቸው ይህ የተንጣለለ ሣር ከየት የመጣ ነው የሚለውን ለማወቅ ነበረ።

“ያገኘነው ውጤት እጅግ በጣም አስደነቀን” ትላለች የጥናቱ ዋና አዘጋጅ ጄን ኤጅሎ።

“አንድ የዕፅዋት ዝርያ 180 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ስፍራ ላይ ተንጣሎ ይገኛል። ይህም በዓለማችን ትልቁ ያደርገዋል።”

ሌላው አስደናቂው የዚህ ሣር ተፈጥሮ በተለያዩ ቦታዎች በተለያየ ቀለምና አፈጣጠር ተጣምሮ መኖሩ ነው።

“በጣም ችግርን መቋቋም የሚችል ተክል ነው። በተለያዩ የአየር ንብረቶች ውስጥ መኖር የሚችል ነው። ሌሎች ዕፅዋት ግን ይህን ማድረግ አይችሉም” ይላሉ ከአጥኚዎቹ አንዱ የሆኑት ዶክተር ኤሊዛቤት ሲንክሌር።

ይህ ሣር በተለምዶ ሰርዶ የሚባለውና ውስጥ ለውስጥ እስከ 35 ሴንቲሜትር የሚያድገው የሣር ዝርያ ነው።