በእስራኤል የአየር ጥቃት የጋዛ ሆስፒታል መመታቱን የሃማስ ጤና ሚኒስቴር ገለፀ

በጋዛ ከተማ የሚገኘው ትልቁ የሕክምና ተቋም አል አህሊ ሆስፒታል በእሳት ተያይዞ ይታያል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

እስራኤል በፈጸመችው የአየር ጥቃት በጋዛ ከተማ የሚገኝ ሆስፒታል በከፊል መውደሙን የሃማስ ጤና ሚኒስትር ገለፀ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምስል ባለ ሁለት ፎቁ ሆስፒታል በሚሳዔል ከተመታ በኋላ በእሳት ሲያያዝ ይታያል።

በአካባቢው የነበሩ ሰዎች፣ በሆስፒታሉ ተኝተው እየታከሙ የነበሩ ሕሙማን ራሳቸውን ለማዳን ሲሸሹ ይታያል።

የዓይን ምስክሮች በአየር ጥቃቱ በጋዛ ከተማ ትልቅ የሆነው የአል አህሊ ሆስፒታል የጽኑ ሕሙማን እንዲሁም ቀዶ ሕክምና የሚካሄድባቸው ክፍሎች መውደማቸውን ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስትሩ ሕንጻው "ሙሉ በሙሉ ወድሟል" ያሉ ሲሆን ይህም "ሕሙማን እና የሆስፒታሉ ባልደረቦች እንዲፈናቀሉ አድርጓል" ብሏል።

ሃማስ በእስራኤል የተፈጸመውን ጥቃት "አሰቃቂ ወንጀል" ሲል ገልጾ ተጨማሪ መረጃዎችን እያጣራሁ ነው ብሏል።

አንድ በአካባቢው የሚገኝ ጋዜጠኛ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ለአንድ የሕክምና ባለሙያ ስልክ ደውሎ አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቁን ተናግሯል።

እንደ ጋዛ የሲቪል ድንገተኛ አደጋ አገልግሎት መረጃ በጥቃቱ በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት የለም።

በሆስፒታሉ ውስጥ ሲሰራ የነበረው ሌላ ጋዜጠኛ የእስራኤል ጦር መኮንን በድንገተኛ ክፍል ውስጥ ለሚሰራ ዶክተር ጋር በመደወል ሆስፒታሉን በአስቸኳይ ለቅቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቁን ተናግሯል።

ኦፊሰሩ በስልክ መልዕክቱ "ሁሉም ታካሚዎች እና ተፈናቃዮች ከአካባቢው ርቀው መሄድ አለባቸው" ማለቱን ተናግሯል።

"አካባቢውን ለቅቆ ለመውጣት 20 ደቂቃ ብቻ ነው ያለህ።"

በማኅበራዊ ድረጾች ላይ በሚዘዋወሩ ምስሎች ሠራተኞቹ እና ሕሙማን በጨለማ ሕንጻውን ለቅቀው ሲወጡ ይታያል።

በተጨማሪም ሴቶች እና ሕጻናትን ጨምሮ በርካታ ፍልስጤማውያን ተጠልለው ከነበሩበት የሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ወጥተው ሲሸሹ ታይተዋል።

ከጦርነቱ በፊት ትንሽ የሕክምና ተቋም የነበረው አል-አህሊ፣ በጋዛ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የአል-ሺፋ የሕክምና መስጫ ተቋም እና በሰሜናዊ የጋዛ ሰርጥ የሚገኙ ሆስፒታሎች ከወደሙ ወዲህ ትልቁ የሕክምና አገልግሎት አቅራቢ ሆኗል።

በሃማስ የሚመራው የመንግሥት ማስታወቅያ ቢሮ በመግለጫው ጥቃቱን አውግዟል።

ሃማስ በመግለጫው እስራኤል "በመቶ የሚቆጠሩ ሕሙማንን እና የሕክምና ባለሙያዎችን የያዘውን የአል-አህሊ ሆስፒታልን ዒላማ በማድረግ አሰቃቂ ወንጀል እየፈፀመች ነው" ብሏል።

እአአ በጥቅምት 2023 በተመሳሳይ ሆስፒታል ላይ በተፈጸመ ጥቃት በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎችን ተገድለዋል።

የፍልስጤም ባለስልጣናት ለፍንዳታው የእስራኤልን ጥቃት ተጠያቂ አድርገዋል።

እስራኤል በበኩሏ ፍንዳታውን የደረሰው የፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ ታጣቂ ቡድን ያልተሳካ ሮኬት የማስወንጨፍ ሙከራ ነው ስትል አስተባብላለች።

ሐማስ መስከረም 26/2016 በፈጸመው ጥቃት 1,200 ሰዎች ሲገደሉ፤ 251 ሰዎች ደግሞ ታግተው ተወስደዋል።

በሐማስ የሚመራው ጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው ከዚህ ጥቃት በኋላ ከ60 ሺህ ገደማ ሰዎች በእስራኤል ጥቃት ጋዛ ውስጥ ተገድለዋል።

ከእነዚህም መካከል 1,563 ፍልስጤማውያን ከመጋቢት 18 ጀምሮ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ አጠናክራ በቀጠለችው የአየር እና የምድር ወታደራዊ እርምጃ የተገደሉ መሆናቸውን የሃማስ ጤና ሚኒስትር ይናገራል።

ባለፈው ጥር ወር የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት መጋቢት ላይ ተጥሷል። በአሁኑ ውቅት በጋዛ 58 ታጋቾች ያሉ ሲሆኑ፤ ከመካከላቸውም 24ቱ በሕይወት አሉ ተብሎ ይታመናል።