የእስራኤል ብሔርተኞች በሙስሊሞች መኖሪያ መንደር ሰንደቅ ዓላማ ይዘው መውጣታቸው ቁጣን ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በምስራቅ እየሩሳሌም የሙስሊም መንደሮች በሺህዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ሰንደቅ ዓላማ እያወለበለቡ ሠልፍ መውጣታቸው በፍልስጤማውያን ዘንድ ቁጣ አስነሳ።
የፍልስጤም ፕሬዝዳንት ደግሞ እስራኤል "በእሳት እየተጫወተች ነው" ሲሉ ጉዳዩን ገልጸውታል።
እስራኤላውያኑ በከፍተኛ ቁጥር በሙስሊም መንደሮች ሰልፍ ያደረጉት የሰው ሕይወት መጥፋትን ያስከተለ ግጭት ተከስቶ ውጥረት ባየለበት ወቅት ነው።
ሠልፉ እአአ በ1967 በተካሄደው ጦርነት እስራኤል ምስራቅ እየሩሳሌምን ጠቅልላ መያዟን ለመዘከር ነው።
እስራኤል እየሩሳሌምን ዋና ከተማዋ አድርጋ ብትመለከትም በፍልስጤማዊያን እና በአብዛኛዎቹ ሃገራት ውድቅ ይደረጋል።
ፍልስጤማውያን እስራኤል የተቆጣጠረችው ምስራቅ እየሩሳሌም የወደፊቷ ዋና ከተማቸው እንደሆነች ይገልጻሉ። ይህም በእስራኤል ውድቅ ይደረጋል።
በጥንታዊቷ ከተማ የደማስቆ በር መግቢያ ላይ ወጣት እስራኤላውያን ሰንደቅ ዓላማ ይዘው ከበሮ በመደለቅ እየጨፈሩ ወደ ሙስሊሞች ሰፈር ሲያመሩ ሁኔታው አስጨናቂ ነበር ተብሏል።
ፍልስጤማውያን እነዚህን ድርጊቶች እንደ ግጭት አቀጣጣይ ሲቆጥሩት ታጣቂ ቡድኖች ደግሞ እንደማይታገሡት አስጠንቅቀዋል።
አንዳንድ አይሁዳውያን እስራኤላውያን ቤተሰቦች የሚገፉ የህጻናት ወንበሮችን ይዘው ከተሰበሰበው ሕዝብ መካከል ታይተዋል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የእስራኤል ፖሊሶች ሂደቱን በትኩረት ሲከታተሉ ታይተዋል።
ብዙ ቁጥር ያላቸው ፍልስጤማውያን በሚኖሩበት ሰፈር በሰዓቱ በጣት የሚቆጠሩ የፍልስጤም ጋዜጠኞች የነበሩ ሲሆን ወደ ስራ የሚሄዱ ወይም ቤታቸው ደጃፍ ሆነው ጉዳዩን የሚመለከቱም ነበሩ።
"የፍልስጤም ፕሬዝደንት ቃል አቀባይ ነቢል አቡ ሩዴኔህን “እስራኤል ኃላፊነት በጎደለው እና በግዴለሽነት ሰፋሪዎች በምስራቅ እየሩሳሌም ቅዱሳን ስፍራዎችን እንዲያረክሱ በማድረግ በእሳት እየተጫወተች ነው" ማለታቸውን ተዘግቧል።
የፍልስጤም ባለስልጣናት በሙስሊሞች እና በአይሁዶች ዘንድ የተከበረውን ቅዱስ ስፍራ የሚጎበኙ እስራኤላውያንን እንደ ሰፋሪዎች እና እዚያ መገኘታቸውን እንደ ርኩሰት ይቆጥራሉ።
አይሁዶች እና ሌሎች ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች ቦታውን ለተወሰነ ጊዜ እንዲጎበኙ ቢፈቀድላቸውም ግቢውን ከሚያስተዳድረው የሙስሊም ባለስልጣናት ጋር በተደረገ ስምምነት መሠረት መጸለይም ሆነ ማንኛውንም ሃይማኖታዊ ምልክት ማሳየት የተከለከለ ነው።
በሙስሊሞች ዘንድ ቦታው ሃራም አል ሻሪፍ በመባል የሚታወቅ ሲሆን በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ሦስተኛው ቅዱስ ቦታ የሚባለውን አል-አቅሳ (ቂብሊ) መስጊድ የያዘ ነው። በአይሁዶች ዘንድ ደግሞ ቴምፕል ማውንት የተቀደሰ ስፍራ ነው።












