አዲስ አበባ ውስጥ ፍቅረኛውን በእሳት አቃጥሎ ለሞት ያበቃት ተከሳሽ ሞት ተፈረደበት

የፎቶው ባለመብት, YAECOB NIGUSE
ባለፈው ዓመት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የፍቅር ጓደኛውን በመደብደብ እና ሳኒታይዘር በማርከፍከፍ በእሳት እንድትቃጠል በማድረግ ለህልፈት የዳረገው ግለሰብ ላይ ፍርድ ቤት የሞት ቅጣት ወሰነ።
የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዳግማዊ አራጋው የተባለው ግለሰብ በፈጸመው ከባድ የግድያ ወንጀል በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የሰው ግድያ እና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ክስ መስርቶ ጉዳዩ ሲታይ ቆይቶ ነው ዛሬ ሐሙስ ጥር 18/2015 ዓ.ም. ብይኑ የተሰጠው።
በዚህም ተጠርጣሪው የቀረበበትን ከባድ የወንጀል ድርጊት ክስ ማስረጃዎች መከላከል ባለመቻሉ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሰው ግድያ እና ከባድ ውንብድና የወንጀል ችሎት የሞት ቅጣት ውሳኔ ማሳለፉን የፍትሕ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ተከሳሽ ዳግማዊ አራጋው፣ ሰብለ ንጉሤ የተባለችውን ጓደኛውን ቅዳሜ ታኅሣሥ 30/2014 ዓ.ም ሌሊት በተፈጸመባት ጥቃት እና በእሳት የመቃጠል ጉዳት ለከባድ ስቃይ ተዳርጋ እንደነበር ቤተሰቦቿ በወቅቱ ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።
ሰብለ ላይ በእሳት መቃጠል ብቻ ሳይሆን ድብደባ እና በስለት መወጋትም የደረሰባት ሲሆን፣ ሰብለ ለቀናት ሆስፒታል ውስጥ ህክምና ሲደረግላት ቆይታ፣ ቃጠሎው ኢንፌክሽን ፈጥሮ በሰውነቷ ላይ ከባድ የጤና መቃወስ በማስከተል ሕይወቷ አልፏል።
ተከሳሹ ዳግማዊ አራጋው ወንጀሉ በተፈጸመበት ዕለት አብራው የምትኖረውን ሟች ሰብለ ንጉሤን በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት ከባድ ድብደባ፣ የተለያዩ የአካል ክፍሏ ላይ ደግሞ በስለት መውጋት እና ተቀጣጣይ የሆነውን ሳኒታይዘር ሰውነቷ ላይ በማርከፍከፍ ክብሪት ለኮሷ እንድትቃጠል ማድረጉ ተገልጿል።
ተከሳሽ ክሱ ለችሎቱ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አልፈጸምኩም ብሎ የተከራከረ ቢሆንም፣ ዐቃቤ ሕግ ወንጀሉን የሚያስረዱ ሰው ምስክሮች አቅርቦ ለፍርድ ቤቱ ያሰማ ሲሆን በተመሳሳይም የሰነድ ማስረጃዎችንም ማቅረቡ ተገልጿል።
ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ እንዲከላከል በሰጠው ብይን መሠረት የሰው እና የሰነድ ማስረጃ እንዳለው ቢገልጽም ከሰው ምስክር ውጪ የተባለው የሰነድ ማስረጃ አለመገኘቱ ለፍርድ ቤቱ የቀረበው ምላሽ አመልክቷል።
በዚህም መሠረት ተከሳሽ የቀረበበትን የወንጀል ድርጊት ክስ መከላከል ሳይችል ቀርቶ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሰው ግድያ እና ከባድ ውንብድና የወንጀል ችሎት በሞት እንዲቀጣ ወስኗል።












