በጀልባ የሚመጡ ስደተኞች ቁጥር ማሻቀብ ያሳሰባት ጣሊያን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀች

የፎቶው ባለመብት, EPA
በርካታ ስደተኞችን የያዙ ጀልባዎች መጉረፋቸው ያሳሰባት ጣሊያን ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀች።
የጣሊያን ሚኒስትሮች ከሰሜን አፍሪካ በሜድትራንያን ባህር አቋርጠው ወደ አገሪቱ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንም ተከትሎ ነው ይህንንም ለመቀነስ ውሳኔውን ያስተላለፉት።
በባለፉት ሶስት ቀናት ውስጥ ሶስት ሺህ ያህል ስደተኞችም ወደ ጣሊያን ገብተዋል።
በርካታ ጀልባዎች በጣሊያኗ ደሴት ላምፑዴሳ ያረፉ ሲሆን የባህር ዳርቻ ጠባቂዎች ከባለፈው ሳምንት አርብ ጀምሮ 2 ሺህ የሚደርሱ ስደተኞችን መታደግ ችለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከአውሮፓውያኑ 2017 ወዲህ ከፍተኛውን የስደተኞችን ሞት መመዝገቡን አስታውቋል።
የተመድ አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ከጥር ወር ጀምሮ ባሉ ሶስት ወራት ውስጥ 441 ሰዎች በማዕከላዊ ሜድትራንያን ባህር ውስጥ መሞታቸውን ገልጿል።
አገራት ለነፍስ አድን በሚያደርጉት መዘግየት ምክንያት ቢያንስ 127 ሰዎች ህይወታቸው እንዲቀጠፍ ምክንያት መሆኑን ያስጠነቀቀ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪም ስደተኞቹ ሙሉ በሙሉ ምላሽ በመነፈጋቸውም ህይወታቸው አልፏል።
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በቱኒዝያ ሁለት የስደተኞች ጀልባ ሰጥመው ቢያንስ አራት ስደተኞች ሲሞቱ ከ20 በላይ ጠፍተዋል። የጀርመን የረድዔት ድርጅት ሬስኪሺፕ የ22 ስደተኞችን ህይወት መታደግ እንደቻለና ወደ ላምፔዱሳ ደሴት መወሰዳቸውን አስታውቋል።
ቱኒዝያ በቅርብ ወራት ውስጥ ለበርካታ የስደተኛ ጀልባዎች መነሻ የሆነች ሲሆን ቅዳሜ የደረሰው አደጋ በባህርዳርቻው ላይ ከተከሰቱት በርካታ አደጋዎች ውስጥ የቅርቡ ነው።
የጣሊያኗ ላምፔዱሳ ደሴት ከቱኒዝያዋ የስፋክስ ወደብ በ185 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።
የጣሊያን የቀኝ ክንፍ ጥምር መንግሥት መደበኛ ያልሆነ ስደትን ለመግታት እየጣረ ቢሆንም ወደ አገሪቱ የሚገቡ ስደተኞች ካለፈው አመት ከነበረው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
ረቡዕ ከሰዓት በኋላ 700 የሚሆኑ ስደተኞችን የጫነች የአሳ ማጥመጃ ጀልባ በሲሲሊ ወደብም ትደርሳለች ተብሏል።
የባህር እና ሲቪል ጥበቃ ሚኒስትር ኔሎ ሙሱሜቺ በአገሪቱ ያለው የስደተኞች ፍሰት 300 በመቶ በማሻቀቡ ምክንያት የጣሊያንን መሰረተ ልማት አደጋ ጋርጦበታል ብለዋል።
“ፍጹም ድንገተኛ ነው። ከዚህ በፊትም አይተነውም አናውቅም። ስደተኞቹ የሚደርሱባቸው ደሴቶቻችን ብቻ ይህንን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መቋቋም አይችሉም." ብለዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ችግሩን አይፈታውም በማለት ያሳሰቡት ሚኒስትሩ የአውሮፓ ህብረት ኃላፊነት በተሞላ መልኩም ጣልቃ እንዲገባም ጠይቀዋል።
ከተጨማሪ 5 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ ጣሊያን ያስተላለፈችው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውሳኔ በሜድትራንያን ባህር እያሻቀበ የመጣውን የስደተኞችን ቁጥር እንዴት እልባት እንደሚያገኝለት ግልጽ አይደለም።
ነገር ግን ሪፖርቶች እንደሚያሳዪት ስደተኞችን የመቀበሉን ሂደት ማፋጠንና በጣሊያን ለመቆየት ፈቃድ ያላገኙትንም ወደ አገራቸው እንደሚመልሱ ተነግሯል።












