ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዩክሬን ተዋጊዎች በሩሲያ ተዋጊዎች ላይ ብልጫ ማሳየታቸው ተገለጸ
ባለፈው ሳምንት በተካሄደ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ፣ የዩክሬን ኃይሎች በሩሲያ ሠራዊት ላይ ስምንት ለአንድ የሆነ ብልጫ ማሳየታቻቸውን በዩክሬን ያሉ የሩሲያ ከፍተኛ ባለሥልጣን አስታወቁ።
የሩሲያው ከፍተኛ ባለሥልጣን ቪታሊ ጋንቾቭ ለሩሲያ ቴሌቭዥን በሰጡት ቃል፣ የዩክሬን ወታደሮች በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ያሉ መንደሮችን እንደያዙና በሩሲያ ድንበር በኩል ዘልቀው እንደገቡ ተናግረዋል።
ዩክሬን ወደ 3,000 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚጠጋ አካባቢን ከሩሲያ ኃይሎች ማስመለሷን ገልጻለች።
ይህም ስድስት ወራት በሞላው ጦርነት ከፍተኛ ድል ነው።
ቢቢሲ እነዚህን ቁጥሮች በገለልተኛ ወገን አላጣራም።
የዩክሬን መከላከያ እንደሚለው፣ ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ በአገሪቱ ሰሜን ምሥራቃዊ አካባቢ ማደረገው መልሶ ማጥቃት 20 መንደሮችን ከሩሲያ ይዞታ አስለቅቆ ተቆጣጥሯል።
የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) መከላከያ ባለሥልጣናት እንዳሉት፣ የዩክሬን ወታደሮች ድል በሩሲያ አጠቃላይ ወታደራዊ ዘመቻ ላይ “ትልቅ ትርጉም” ያለው ነው።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ በበኩላቸው፣ በዩክሬን የሚካሄደው ዘመቻ “መጀመሪያ ላይ የተያዘው ዕቀድ ግቡን እስከሚመታ” ይቀጥሏል።
ዩክሬን በቅርቡ በቁጥጥሯ ሥር ባስገባቻቸው ቦታዎች የሩሲያ ኃይሎች ጥቃት ሲፈጽሙ እንደነበር ተገልጿል።
ጥቃት ተከፍቶባቸው ከነበሩ እና ዩክሬን መልሳ ከያዘቻቸው ቦታዎች መካከል ኢዝዩም እና ኩፒዘንስክ ይገኙበታል።
ሩሲያ ኃይሎቿ ከእነዚህ ከተማዎች ሸሽተው “መልሰው እንደተሰባሰቡ” አረጋግጣለች።
ሩሲያ ወታደሮቿ ያጋጠማቸውን መሰናክል ለመበቀል የንጹሀን ዜጎችን መሠረተ ልማት አጥቅታለች በሚል ተወንጅላለች።
ሞስኮ ትላንት ወደ ዩክሬን ሚሳኤል ተኩሳ የኃይል መስመር ተቋርጧል።
ይህ የኃይል መቆራረጥ በኪዬቭ እና ዶንተስክ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ጫና አሳድሯል።
የኪዮቭን የኤሌክትሪክ አቅርቦት በድጋሚ ማስጀመር ተችሏል።
የዩክሬኑ ፖለቲከኛ ኢልሆር ተርኮቭ የሩሲያን ጥቃት “የዩክሬን ወታደሮች ስኬትን ተከትሎ በመጣ ንዴት የተነሳሳ በቀል” ብለውታል።
የዩክሬን የመከላከያ ሚኒስትር ኦሌክሲ ረቭኒኮቭ እንዳሉት፣ አሁን ላይ ዋነኛ ግባቸው ዩክሬን ያስመለሰቻቸውን አካባቢዎች መጠበቅ ነው።
ሩሲያ ጦርነቱ ከተጀመረበት ሳምንት ጀምሮ ይዛቸው ከነበሩ አካባቢዎች ስትወጣ በርካታ መሣሪያዎችን ጥላ ነው።
የሩሲያ ታንክ አምራች ድርጅት ምርቶቹን በከፍተኛ ፍጥነት እየሠራ እንደሆነ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።
ዩራልቫጎዛቮድ የተባለው የሩሲያ ከፍተኛ የወታደራዊ ተሽከርካሪዎች አምራች፣ አሁን ባለው ከፍተኛ የምርት ፍላጎት ምክንያት እረፍት እንዳይወስድ መደረጉንም ሪፖርቶች አሳይተዋል።