የቻይና “የስለላ”ፊኛ በርካታ አገራትን ኢላማ ማድረጉን የአሜሪካ ባለሥልጣናት ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ በግዛቷ ውስጥ ተኩሳ የጣለችው እና የስለላ ነው ተብሎ የተጠረጠረው የቻይና ፊኛ አምስት አህጉራትን ያካለለና ተመሳሳይ ተልዕኮ ያላቸው መርከቦች አካል ነው ብላ እንደምታምን ገለጸች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፣በዚህ ሰፊ ፕሮግራም ኢላማ የሆነችው አሜሪካ ብቻ አይደለችም ብለዋል።
በመሆኑም አሜሪካ ከተሰባበረው ፊኛ ያገኘችውን መረጃ ለሌሎች በርካታ አገራት ማጋራቷንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ቻይና ፊኛው ለስለላ ተልዕኮ ጥቅም ላይ እንዳልዋለ እና የአየር ሁኔታ ጥናት ለማካሄድ የሚያገለግል የአየር መርከብ ነው ስትል በተደጋጋሚ ገልጻለች።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንዳሉት ፊኛው 200 ጫማ (60 ሜትር) ቁመት ያለው ሲሆን የመጫን አቅሙ አነስተኛ አውሮፕላኖች ጋር ይስተካከላል።ክብደቱም በመቶዎች አሊያም በሺዎች ፓውንድ ይመዝናል።
ይህ ፊኛ ቅዳሜ ዕለት በደቡብ ካሮላይና የባሕር ዳርቻ በተዋጊ ጄት ተመትቶ ተጥሏል።
ውሳኔው በአገራቱ መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያሻከረ ሲሆን አንቶኒ ብሊንከን በዓመታት ውስጥ በቻይና እና በአሜሪካ መካከል ለሚካሄድ ከፍተኛ ስብሰባ ወደ ቻይና ሊያደርጉት የነበረውን ጉዞ እንዲሰርዙ አስገድዷል።
ዋሽንግተን ፖስት ስማቸውን ያልጠቀሳቸውን ባለሥልጣናት ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው፣ የስለላ ነው ተብሎ የተጠረጠረው ፊኛ የተለቀቀው በቻይና የባህር ዳርቻዋ ግዛት ሃይናን ሲሆን ጃፓን፣ ሕንድ፣ ቬየትናም፣ ታይዋን እና ፊሊፒንስን ኢላማ አድርጓል ብላ አሜሪካ እንደምታምን ዘግቧል።
ረቡዕ ዕለት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫም የመከላከያ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ብርጋዲየር ጀኔነራል ፓት ራይደር፣አሜሪካ ተመሳሳይ ፊኛዎች በሰሜንና በደቡብ አሜሪካ ፣ በደቡብ ምሥራቅ እስያ ፣ በምሥራቅ እስያ እና አውሮፓ ላይ ሥራ ላይ ውለው ነበር ብላ እንደምታምን ተናግረዋል።
ጄነራል ራይደር “ስለ እነዚህ ፊኛዎች እና እነሱን እንዴት መከታተል እንደሚቻል ብዙ ተምረናል” ሲሉ አሜሪካ እንደዚህ ዓይነት ፊኛዎችን የመከታተል አቅም እንዳላት አረጋግጠዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም ፊኛዎቹ ሁሉም ለስለላ ተልዕኮ ጥቅም ላይ የዋሉ ቢሆንም በመጠናቸው እና በችሎታቸው ግን ልዩነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
አሜሪካ ፊኛዎቹ በአሜሪካ የአየር ክልል አራት ጊዜ ጥቅም ላይ እንደዋሉ ብታምንም፣ ጀነራሉ ግን በዚህ ላይ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።
ዋሽንግተን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ስለዚህ የስለላ ፕሮግራም ለ40 አጋር አገራት ገለጻ ማድረጓን የባይደን አስተዳደር አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ መናገራቸውን ዘግቧል።
የባሕር ኃይሎች እና የባሕር ዳርቻ ጥበቃ መርከቦች እንዲሁም ጠላቂዎች አሁንም የፊኛውን ስብርባሪ እየፈለጉ ነው።
ምንም እንኳን ባለሙያዎች የፊኛው ስብርባሪ ባለሥልጣናት ፊኛው ምን ማድረግ እንደሚችል እና መረጃ እንዴት እንደሚያስተላልፍ በተሻለ ሁኔታ ለማወቅ እንደሚረዳቸው ቢናገሩም፣ አሜሪካ ከስብርባሪው ምን የደኅነንት መረጃ እንዳገኘች እስካሁን ግልጽ አይደለም።












