በትራምፕ እና በስቶርሚ ዳንኤልስ መካከል የተፈጠረው ምንድን ነው?

ታትሟል

የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስቶርሚ ዳንኤልስ ከተባለችው የልቅ ወሲብ ተዋናይት ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት ዝም ለማሰኘት ገንዘብ ከፍለዋታል መባሉን ተከትሎ የወንጀል ክስ ሊመሰረትባቸው ነው።

ዳንኤልስ ከትራምፕ ጋር የወሲብ ግንኙነት መፈጸሟን እና ከ2016ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በፊት ስለጉዳዩ ላለማውራት ተስማምታ ከትራምፕ ጠበቃ 130ሺህ ዶላር መቀበሏን ገልጻለች።

የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጠበቃ ማይክል ኮሀን ፍርድ ቤት ቀርቦ በትራምፕ ትዕዛዝ ክፍያውን መፈጸሙን አምኗል። ማይክል ኮሀን በትራምፕ አስተዳደር ወቅት በተለያዩ ክሶች ጥፋተኛ ተብሎ ለሁለት ዓመታት በእስር ቆይቷል።

ትራምፕ ግን ከስቶርሚ ዳንኤልስ ጋር ጾታዊ ግንኙነት በጭረሽ አላደረኩም ይላሉ።

የዳንኤልስ አደባባይ መውጣት

ትራምፕ ከቀድሞ የልቅ ወሲብ ተዋናይት ጋር ግንኙነት አላቸው የሚለው መረጃ መናፈስ የጀመረው እአአ 2018 ላይ ነበር።

ትክክለኛ ስሟ ስቴፈኒ ክሊፎርድ የሆነው ስቶርሚ ዳንኤልስ በመገናኛ ብዙኃን ላይ እየቀረበች ከትራምፕ ጋር እአአ 2006 ላይ ወሲብ መፈጸማቸውን ተናግራለች።

ዳንኤልስ ከትራምፕ ጋር ለእርዳታ ድርጅት ተብሎ በተዘጋጀ የጎልፍ ውድድር ላይ ከተገናኙ በኋላ በትራምፕ የሆቴል ክፍል ውስጥ ወሲብ መፈጸማቸውን ትገልጻለች።

በወቅቱ ከግንኙነታቸው በኋላ ስለጉዳዩ እንዳትናገር ከትራምፕ ማስፈራሪያ ደርሷት እንደነበረ ስትጠየቅ፤ “ጉዳዩ ያሳሰበው አይመስልም ነበር። ትዕቢተኛ ነገር ነበር” በማለት ዳንኤልስ መልሳለች።

ትራምፕ እና ዳንኤልስ በተገናኙበት የጎልፍ ውድድር ላይ የትራምፕ ባለቤት ሜላኒያ ትራምፕ አልተገኘችም ነበር። ወሲብ ፈጽመውበታል በተባለበት ወቅት ሜላኒያ ገና መውለዷ ነበር።

ማስፈራሪያ እና ክፍያ

ትራምፕ ያሸነፉበት የ2016 የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከመካሄዱ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ስለ ግንኙነታቸው ምንም እንዳትል በጠበቃ ማይክል ኮሀን አማካይነት ከትራምፕ 130ሺህ ዶላር መቀበሏን ዳንኤልስ ትናገራለች።

ዳንኤልስ ገንዘቡን የተቀበልኩት ለእራሴ እና ለቤተሰቤ ደኅንነት ስለሰጋው ነው ትላለች።

ዳንኤልስ ስለጉዳዩ ቃል እንዳታወጣ ሕጋዊ መንገድ እንዲሁም አካላዊ ማስፈራሪያ ይደርስብኝ ነበር ብላለች።

ከትራምፕ ጋር ስለነበራት ግንኙነት ከአንድ መገናኛ ብዙኃን ጋር ቃል መጠይቅ ለማድረግ ከስማማች በኋላ አንድ ግለሰብ እርሷን እና ጨቅላ ሕጻኗን ቀርቦ እንዳስፈራራት ገልጻለች።

ዝም ለማሰኘት ክፍያ መፈጸም ወንጀል ነው?

በግለሰቦች መካከል ወይም በግለሰብ እና በድርጅት መካከል ግንኙነት ከተቋረጠ በኋላ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዳይሰጥ ከፍያ መፈጸም ወንጀል አይደለም።

ይሁን እንጂ ትራምፕ ክፍያውን የፈጸሙት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ሊካሄድ ጥቂት ሳምንታት እየቀሩት ስለሆነ፤ የቀድሞ ፕሬዝዳንት እርምጃ የምርጫ ቅስቀሳ ጥሰት ጋር የሚስተካከል ነው በማለት የሚከራከሩ አሉ።

እአአ 2018 ላይ የምርጫ ቅስቀሳ የፋይናንስ ሥርዓት ጥሰቶችን ጨምሮ ሌሎች ወንጀሎችን መፈጸሙን ያመነው የትራምፕ ጠበቃ ማይክል ኮሀን፣ በቀድሞ ፕሬዝዳንት ትዕዛዝ ገንዘብ ለዳንኤልስ መክፈሉን ለፍርድ ቤት ተናግሯል።

ኮሀን ለዳንኤልስ ክፍያ ከፈጸመ በኋላ የከፈለው ገንዘብ በትራምፕ እንደተተካለት ጨምሮ ቃሉን ሰጥቷል።

ትራምፕም ቢሆኑ ኮሀን ወጪ ያደረገውን 130ሺህ ዶላር እንደከፈሉት ቢያምኑም፤ ከዳንኤልስ ጋር የተቃራኒ ጾታ ግንኙነት እንደሌላቸው እና የምርጫ የፋይናንስ ሕጎችን አለመጣሳቸውን ይከራከራሉ።

ይሁን እንጂ የትራምፕን ጉዳይ ሲመረምሩ የቆዩት ዳኞች በቀድሞ ፕሬዝዳንት ላይ የወንጀል ክስ እንዲመሰረት ድምጽ ሰጥተዋል።

ትራምፕ ግን ክሱ ፖለቲካዊ ነው ከማለታቸውም በተጨማሪ የቀጣዩን የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት ለማስቀየር ክሱ እንደተቀነባበረባቸው ይገልጻሉ።