እስራኤል ፍልስጤማዊውን ጠበቃ ወደ ፈረንሳይ አባረረች

የፎቶው ባለመብት, AFP
የእስራኤል የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስቴር ፍልስጤማዊ-ፈረንሳያዊ የሰብዓዊ መብት ተሟጋችን ወደ ፈረንሳይ እንዲሰናበት መደረጉን አስታወቀ።
የ37 ዓመቱ ሳላህ ሃሞኡሪ በእስራኤል ባለስልጣናት የደኅንነት ስጋት ነው ከተባለ በኋላ በፖሊስ ታጅቦ ወደ ፈረንሳይ በሚበር አውሮፕላን ላይ እንዲሳፈር ተደርጓል።
የአገሪቱ ባለስልጣናት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹን የአሸባሪ ድርጅት አባል ነው ብለው ከከሰሱት በኋላ የእየሩሳሌም ነዋሪነቱን እንዲነጠቅ ተደርጓል።
ሃሞኡሪ የቀረበበትን ክስ የሚያጣጥል ሲሆን፤ ግለሰቡ በኃይል ከመኖሪው እንዲባረር መደረጉን የመብት ተቆርቋሪዎች እና ፈረንሳይ ኮንነውታል።
የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ እንዲባረር መደረጉ ሕጋዊ መሠረት የለውም ብሏል።
የእስራኤል የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስቴር ግን ሳለህ ሃሞኡሪ “በዜጎች እና ተዋቂ እስራኤላውያን ላይ የሽብር ጥቃት ለማድረስ አቅዷል እንዲሁም አስተባብሯል” ይላል።
ሃሞኡሪ እስራኤላዊ ዜግነት የለውም። የእየሩሳሌ ሕጋዊ ነዋሪ ግን ነበር። በወላጅ እናቱ ምክንያት ደግሞ የፈረንሳይ ዜግነት አለው።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ በእስራኤል መንግሥት አሸባሪ ተብሎ ለተፈረጀ አዳሜር ለተባለ ተቋም ይሰራል። ይህ ተቋም ለፍልስጤማውያን የሕግ ድጋፍ በማድረግ እና እስር ላይ ላሉ ሰዎች ጥብቅና በመቆም ይታወቃል።
ታዲያ እስራኤል ይህን ተቋም ጨምሮ አምስት የሲቪል ድርጅቶችን አሸባሪ ስትል እአአ 2021 ላይ ፈርጃለች።
የአገሪቱ ጦር እነዚህ ተቋማት እስራኤል አሸባሪ ብላ ከመደበችው ‘ፖፑላር ፍሮንት ፎር ዘ ሊብሬሽን ኦፍ ፓላስታይን’ ተዋጊ ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው ይላል።
ሃሙኡሪ ወደ ፈረንሳይ እንዲባረር ከመደረጉ በፊት በተደጋጋሚ ለእስር ተዳርጎ ነበር።
እአአ 2005 ላይ አንድ ፖለቲከኛን ለመግደል አሲሯል ተብሎ 6 ዓመታትን በእስር አሳልፎ ነበር። ከጥቂት ወራት በፊት ደግሞ በአገሪቱ ጦር አዛዥ ትዕዛዝ መሠረት ክስ ሳይመሰረትበት ለወራት በእስር ለማሳለፍ ተገዶ ነበር።
ያለ ክስ ለ4 ወራት የታሰረው ሃሙኡሪ ድጋፍ እንዲሰጡት ለፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ደብዳቤ ጽፎ ነበር። ይህን ተከትሎ እስራኤል ከፍተኛ ጥበቃ ወደሚደረግለት እስር ቤት አዘዋውራው ነበር።
በዚህ ወቅት ሃሙኡሪ ለብቻው ተስሮ በሚገኝበት እስር ቤት ለ19 ቀናት የዘለቀ የረሃብ አድማ አድርጎ እንደነበረ ተዘግቧል።
የግለሰቡን ከአገር መባረር እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያሉ ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ኮንነውታል። አምነስቲ ሃሙኡሪ “የፍልስጤማውያን ጠበቃ ስራው ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሎታል” ብሏል።












