የሳዑዲ አረቢያ ድል በአርጀንቲና ላይ፣ የዓለም ዋንጫው ቀዳሚ ያልተጠበቀ ውጤት

የሳዑዲ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በዓለም እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ይህ ነው የሚባል የጎላ ስም የሌላት ሳዑዲ አረቢያ በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ለፍጻሜው ከሚጠበቁ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነውን የአርጀንቲናን ቡድን ድል አድርጋለች።

እሁድ ዕለት በተጀመረው በዚህ የዓለም ዋንጫ ከማይጠበቁ ክስተቶች ሁሉ ቀዳሚ በሆነ ውጤት፣ የሳዑዲ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ከመመራት ተነስተው የሁለት ጊዜ የዓለም ዋንጫ ባለቤት የሆነችውንና ሜሲን ጨምሮ በባለ ዝናዎች የተዋቀረውን የአርጀንቲናን ቡድን አሸንፈዋል።

ሳዑዲዎች በሉሳይል ስታዲየም ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታቸው አንድ ለባዶ ከመመራት በመነሳት ሁለት ግቦችን አስቆጥረው የምድብ ሐ መሪነት ቦታን ተቆናጠዋል።

በዓለም የእግር ኳስ ደረጃ ላይ 51ኛ የሆነችው ሳኡዲ አረቢያ በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ የተሰጠባትን የፍጹም ቅጣት ምት ሊዮኔል ሜሲ አስቆጥሮ ነው ጨዋታውን እየተመራች የጀመረችው።

በአርጀንቲና በኩል በርካታ ግቦችን ለማስቆጠር ተደጋጋሚ ጥረቶች ተደርገው ተጨማሪ ሦስት ግቦችን ማስቆጠር ቢችሉም ዕድለኛ ሳይሆኑ ቀርተው ከጨዋታ ውጪ በመሆናቸው ሳይመዘገቡላቸው ቀርተዋል።

የጨዋታው ግማሽ ድረስ አርጀንቲና በአንድ ለባዶ ውጤት መሪ ሆና እረፍት ከተደረገ በኋላ፣ ሁለተኛው አጋማሽ ተጀምሮ በ10 ደቂቃ ውስጥ ሳዑዲ ውጤት ቀያሪውን ግብ አስቆጠረች።

የመጀመሪያው ግብ በሳሌህ አል-ሼህሪ ሲመዘገብ፣ ተከትሎ ደግሞ ሳሌም አል ዳወሳሪ ያስቆጠራት ግብ ለአርጀንቲና ድንጋጤን ለሳዑዲዎች ደግሞ ፈንጠዝያን አጎናጸፈች።

አርጀንቲናዎች በመጀመሪያው ጨዋታቸው ተጨማሪ ግቦችን በማስቆጠር ድልን በእጃቸው አሊያም አቻ ለመውጣት ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

በዓለም ዋንጫ ጨዋታ ላይ በአሸናፊነት የተመዘገበላት አራተኛ ጨዋታ ብቻ ያላት ሳዑዲ አረቢያ፤ አርጀንቲናን በመርታት ሜክሲኮ እና ፖላንድ ያሉበትን ምድብ አጓጊ አድርጋዋለች።

የሊዮኔል ሜሲው የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን በዚህ ውድድር ለዋንጫ ከሚጠበቁጥ መካከል ሲሆን፣ ቡድኑ ከዓለም ዋንጫ ቀደም ብሎ ባደረጋቸው 36 ጨዋታዎች ምንም ሽንፈት ካለማስተናገዱ በተጨማሪ፣ ባለፈው ዓመት የአህጉራዊው ኮፓ አሜሪካ ባለድል ነው።

አርጀንቲና ከአውሮፓውያኑ 1986 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫ ለማንሳት ያላት ተስፋ አሁንም የጨለመ ባይሆንም ከባድ ፈተና ይጠብቃታል።

ይህ የዓለም ዋንጫ ለታዋቂው ሊዮኔል ሜሲ የመጨረሻው ሊሆን ይችላል እየተባለ ሲሆን፣ ቡድኑ በሳዑዲ የገጠመውን የሽንፈት ጥላ በመግፈፍ ወደ ቀጣይ ዙሮች አልፎ እንደተጠበቀው ዋንጫ ካነሳ ለሜሴ የክብር ስንብት ይሆንለታል እየተባለ ነው።

አሁን ግን ሳዑዲ አረቢያ በምድብ ሐ ከተመደቡት ቡድኖች ሙሉ ሦስት ነጥብ ከአንድ ንጹህ ጎል ጋር በመያዝ መሪ ሆናለች። አርጀንቲና ደግሞ ካለ ነጥብ በአንድ የግብ ዕዳ ለጊዜው ከምድቡ ግርጌ ተቀምጣለች።

ቅዳሜ ኅዳር 17/2015 ዓ.ም ሳዑዲ አረቢያ ከፖላንድ፣ አርጀንቲና ደግሞ ከሜክሲኮ ቀጣይ ጨዋታ ያደርጋሉ።