ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአውስትራሊያ አየር ማረፊያ ውስጥ ተኩስ የከፈተው ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ዋለ
ትናንት ነሐሴ 8/2014 ዓ.ም. በአውስራሊያ መዲና ካንቤራ በሚገኘ አየር ማረፊያ ተኩስ የከፈተው ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ውሎ ክስ ተመሠረተበት።
ፖሊስ እንዳለው የ63 ዓመቱ ግለሰብ መንገደኞች ሻንጣዎቻቸውን ከሚልኩበት አካባቢ ሆኖ ወደ የአየር ማሪፊያው ሕንጻ መስታወቶች በርካታ ጊዜ ተኩሷል።
ግለሰቡ በከፈተው ተኩስ ጉዳት የደረሰበት ሰው ባይኖርም መንገደኞች ግን በከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ሆነው በአየር ማረፊያ ውስጥ ሲሯሯጡ ታይተዋል።
ጥብቅ የመሳሪያ ይዞታ ሕግ ባለባት አውስትራሊያ በጥይት የሚገደሉ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ነው።
ፖሊስ በስም ያልጠቀውስን ግለሰብ በፍጥነት በቁጥጥር ሥር አውሎ መሳሪያውን መያዙን የገለጸ ሲሆን፤ ግለሰቡ በአየር ማረፊያው ተኩስ ለመክፈት ምን እንዳነሳሳው እስካሁን አልተገለጸም።
በመዲናዋ አየር ማረፊያ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ለጥንቃቄ ሲባል ከአየር ማረፊያው እንዲወጡ የተደረገ ሲሆን በርካታ በረራዎችም ተሰርዘዋል ወይም የበረራ ሰዓታቸው ተቀይሯል።
አውሮፕላን ተሳፍረው ለመብረር በዝግጅት ላይ የነበሩ መንገደኞ በረራ እንዳያደርጉ እግድ ተጥሎባቸው ለሰዓታት በአውሮፕላን ውስጥ ለመቆየት ተገደዋል።
የአውስትራሊያ መገናኛ ብዙሃን ግለሰቡ አምስት ግዜ መተኮሱን የዘገቡ ሲሆን ማሕበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት እየተዘዋወረ ያለ ተንቀሳቃሽ ምስል ደግሞ ፖሊስ ግለሰቡን በቁጥጥር ሥር ሲያውለው አሳይቷል።
በአየር ማረፊያው የነበሩ የዓይን እማኞች በወቅቱ የነበረውን ድንጋጤ እና ግራ መጋባት ተናግረዋል። አንድ መንገደኛ የተኩስ ድምጽ ከሰማች በኋላ ወንበር ስር መደበቋን ለቢቢሲ ተናግራለች።
ሊሊያን ቶምሰን የተባለች የኤቢሲ ጋዜጠኛ የተኩስ ድምጽ ከሰማሁ በኋላ ሰዎች በአየር ማረፊያ ውስጥ ሲሯሯጡ ስመለከት “ችግር” እንዳለ ተገዘንብኩ ትላለች።
ጋዜጠኛዋ አየር ማረፊያ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ፊት ላይ ከፍተኛ ድናጋጤ እና ፍርሃት ይታይ ነበር ብላለች። “ከጠረጴዛ ስር ተደብቀን ቆየን። ፖሊስ ወደ መኪና ማቆሚያ ስፍራ እንድንሄድ እስኪነግረን ድረስ ከጠረጴዛ ስር ተደብቀን ነበር። ገሚሱ ወንበር ስር ተደብቋል ገሚሱ ደግሞ ሲሯሯጥ ነበር። በጣም ያስፈራ ነበር” ስትል በአየር ማረፊያው የነበረውን ሁኔታ ገልጻለች።