ቻይና ከደቡብ ኮሪያ እና ከጃፓን ለሚነሱ ግለሰቦች የቱሪስት ቪዛ መስጠት አቆመች

ታትሟል

ቻይና ለአጭር ጊዜ ቆይታ ከደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ለሚሄዱ ጎብኝዎች ቪዛ መስጠት አቆመች።

ይህ አገራቱ በቻይናውያን መንገደኞች ላይ ለጣሉት የኮቪድ ገደብ የአጸፋ ምላሽ ነው ብላለች።  

በሴኡል የሚገኘው የቤይጂንግ ኤምባሲ እንዳስታወቀው ለጉብኝት ወደ ቻይና ለሚገቡ ደቡብ ኮሪያውያን ቪዛ እንዳይሰጥ ታግዷል። በጃፓን ላይም ተመሳሳይ እገዳ መጣሉን የጃፓን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

አገራቱ በቻይና ላይ የጣሉትን “አግላይ” የሆነውን ገደባቸውን እስከሚያነሱ ድረስም ውሳኔው ጽኑ ሆኖ እንደሚቆይ ቤይጂንግ አስታውቃለች።

ባለፈው ሳምንት ደቡብ ኮሪያ ከቻይና ለሚነሱ መንገደኞች የቱሪስት ቪዛ መስጠት ማቆሟን ያስታወቀች ሲሆን፣ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን እርምጃውን “ተቀባይነት የሌለው” እና “ሳይንሳዊ ያልሆነ” ብሎታል።

የደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ቻይና አሁን ላይ የወሰደችው እርምጃ ተከትሎ አስተያየት በሰጠበት ወቅት ከቻይና በሚነሱ መንገደኞች ላይ የተጣለው ገደብ  “ሳይንሳዊ” እና “ተጨባጭ ማስረጃ” ላይ የተመሠረተ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጿል።

ጃፓን አሁን ላይ ቻይናውያን ጎብኝዎች ከኮቪድ ነጻ መሆናቸውን የሚያሳይ የምርመራ ውጤት በመያዝ ወደ አገሯ እንዲገቡ ፈቅዳለች።

ደቡብ ኮሪያ ከቻይና በሚገቡ መንገደኞች ላይ የቪዛ እገዳ ከመጣሏ አስቀድሞ ከቻይና ወደ አገሪቷ ከገቡት መንገደኞች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ኮቪድ እንደተገኘባቸው የደቡብ ኮሪያ የበሽታ መቆጣጠሪያ ኤጀንሲ ገልጿል።  

ከቻይና የሚነሱ መንገደኞች የሚያርፉበት ሴኡል ኢንቼን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ብቻ ሲሆን፣ መንገደኞች የቫይረሱን መከላከያ በለበሱ የፀጥታ ሠራተኞች ይታጀባሉ።

ቢቢሲም ወደ አየር ማረፊያው የመመርመሪያ ማዕከል ታጅበው የተወሰዱ አንዳንድ መንገደኞችን ማነጋገር ችሎ ነበር።

ከሻንጋይ የተነሳው መንገደኛ ዊሊያም አስተያየቱን ሲሰጥ “ይህ ምንም ማለት አይደለም። በወረርሽኙ ወቅት ከዚህ የከፋ ሁኔታን አሳልፌያለሁ። እንደ መንገደኛ እስከምችለው ድረስ ሕጎችን ለመቀበል እየሞከርኩ ነው” ብሏል።

ዊሊያም ይህን ይበል እንጂ ሌላኛዋ መንገደኛ ግን ሃሳቡን ተቃውመዋለች።

ከሆንግ ኮንግ የተነሳችው ኤሚሊ “እኔ እንደማስበው፣ እርምጃው ሳይንሳዊ አይደለም። ከቻይና የሚገቡ መንገደኞች ብቻ ናቸው እንዲመረመሩ የሚጠየቁት፤ ይህ ፍትሐዊ አይደለም” ብላለች።

በርካታ ደቡብ ኮሪያውያን ግን አገራቸውን በቻይና ካገረሸው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መጠበቅ ይገባል የሚለውን ሃሳብ ይደግፋሉ። ነገር ግን ሁሉም አይደሉም። አንዳንዶቹ ውሳኔው “ሳይንሳዊ ብቻ” ነው ብለው አያምኑም።

ወደ አቡዳቢ እያመራ ያለው ጂንሱን “ፖለቲካው ጉዳይ ያለበት ይመስለኛል። የሁለቱ አገራት ግንኙነት ጥሩ አይደለም። በርካታ ኮሪያውያን ለኮሮናቫይረስ መከሰት ቻይናን ይከሳሉ” ይላል።

ለጫጉላ ሽርሽር ወደ ፓሪስ እያመራች ያለችው ሌላኛዋ መንገደኛ ደግሞ “ደቡብ ኮሪያ ለወረርሽኙ ስጋት የሆነችባት አገር ቻይና ባትሆን ተመሳሳይ ሕግ ላትተገብር ትችላለች” ስትል የጂንሱን ሃሳብ ትጋራለች።

ደቡብ ኮሪያ የጣለችው እገዳዎች ቢያንስ እስከዚህ ወር መጨረሻ ድረስ ይቆያሉ። ይህም ተመራማሪዎች በቻይና አዲስ የተከሰተ የቫይረስ ዝርያ መኖር አለመኖሩን ለማጥናት ጊዜ ይሰጣቸዋል ተብሏል።

በኮሪያ ዩኒቨርሲቲ የተላላፊ በሽታዎች ባለሙያ እና የመንግሥት አማካሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ኪም ዎ ጆ፣ “አሁን ላይ ቻይና ክትትል የምታደርግበት የቫይረስ ዝርያ ስለመኖሩ ግልጽ አይደለም። ከቻይና አዲስ ዝርያ ከተነሳ ለመላው ዓለም አደጋ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጨምረውም “ለኮሪያ የጤና ሥርዓትም አደጋ ነው።አሁን ላይ በርካታ ሆስፒታል የገቡና ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች አሉ። እድሜያቸው የገፉ ሰዎችም ያልተከተቡ ናቸው። ይህ ነው የሚያስጨንቀን” ብለዋል።

አሁን ላይ ከቻይና ወደ ደቡብ ኮሪያ መግባት የሚችሉት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ለሥራ ጉዳይ የሚያመሩ ግለሰቦች አሊያም ዲፕሎማቶች ብቻ ናቸው። እነርሱም ቢሆኑ ከመነሳታቸው በፊት እና በመዳረሻቸው የኮቪድ ምርመራ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በቅርቡ በምርመራ ወቅት ቫይረሱ የተገኘበት አንድ ቻይናዊ ወደ ለይቶ ማቆያ ሆቴል ሲወሰድ ከአውቶብስ ውስጥ ያመለጠ ሲሆን፣ ከሁለት ቀናት በኋላ በሴኡል የሚገኝ ሆቴል ውስጥ በፖሊስ ተይዟል።