ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቻይና ከሦስት ዓመታት በኋላ ድንበሯን ለጎብኚዎች ክፍት አደረገች
ቻይና ከሦስት ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ድንበሬን ለጎብኚዎች ከፍቻለሁ አለች።
ቻይና በመጋቢት 2020 ዓ/ም የኮቪድ ተህዋሲ ወረርሽን ተከትሎ ነበር የጉዞ እግድ የጣለችው።
ከእንግዲህ ገቢ መንገደኞች ማቆያ ስፍራ መቆየት ሳያስፈልጋቸው በቀጥታ መግባት ይችላሉ።
ይሁንና ገቢ መንገደኞች በ48 ሰዓታት ውስጥ የወሰዱትን የክትባት ማስረጃ ማቅረብ ይጠቅባቸዋል።
በርካታ ቤተሰቦች በእገዳው ምክንያት ሳይገናኙ በመቆየታቸው ቻይና ድንበሯን መክፈቷ እንዳስደሰታቸው በመላው ዓለም የሚገኙ ቻይናዊያን ዘንድ ደስታን ፈጥሯል።
ከሆንግ ኮንግ ብቻ በቀጣይ ሳምንታት ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ቻይናዊያን ወደ ቻይና እንደሚገቡ ይጠበቃል።
ከወዲሁ በአየር መንገዶች አካባቢ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሰልፎች እየታዩ ነው።
በርካታ ተጓዦች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ላለፉት ሦስት ዓመታት ብዙ ቤተሰቦች በገደቡ ምክንያት ሳይገናኙ ቆይተዋል።
“ቃላት የለኝም፤ እጅግ ተደስቻለሁ” ያለች አንድ ሌላ ተጓዥ ለሮይተርስ እንደተናገረችው ካንሰር እየተሰቃዩ ያሉ ወላጇን ለሦስት ዓመት ማየት እንዳልቻለች ተናግራለች።
ይህ የጉዞ ገደብ የተነሳበት ወቅት ደግሞ ከቻይናዎቹ አዲስ ዓመት ጋር መገጣጠሙ ትልቅ ፈንጠዚያን ፈጥሯል።
የቻይናዎች አዲስ ዓመት በዓለም ላይ ከፍተኛ የሰዎች እንቅስቃሴ የሚደረግበት ሲሆን በሚሊዯን የሚቆጠሩ ቻይናዊያን ቤተሰባቸውን ለመጠየቅና በዓሉን ለማክበር ከግዛት ግዛት ይንቀሳቀሳሉ። ከአውሮፓና አሜሪካም እንዲሁ በርካቶች ወደ ቻይና የሚያቀኑበት ወቅት ነው።
የቻይና መንግሥት ባወጣው አሃዝ በዚህ አዲስ ዓመት ብቻ 2 ቢሊዮን ጉዞዎች ይደረጋሉ። ይህ ከባለፈው ዘመን ጋር ሲነጻጸር እጥፍ ይሆናል።
የኅብረተሰብ ጤና ባለሙያዎች ይህ ከፍተኛ የሰዎች እንቅስቃሴ በድንገት ክፍት መደረጉ ወረርሽኙን ከቁጥጥር ውጭ ሊያስወጣው ይችላል ይላሉ።
በቻይና አሁንም ቢሆን ከፍተኛ የሆነ የተህዋሲው ስርጭት እንዳለ ይነገራል።
አንድ በጤና ዙርያ ጥናት የሚያደርግ የዩኬ ኩባንያ እንደገመተው በቀን በትንሹ 14ሺህ ሰዎች በቻይና በኮቪድና ኮቪድ ተህዋሲ ባመጣው የጤና መስቅልቅል እየሞቱ ነው።
የዓለም ጤና ድርጅትም ቻይና በኮቪድ የሚሞቱ ዜጎቿን ቁጥር እየደበቀች ነው ሲል መግለጫ አውጥቶ ነበር።
ቻይና ግን ባለፈው ወር የሞቱት 22 ናቸው። ትናንት የሞቱት ደግሞ ሁለት ሰዎች ብቻ ናቸው ትላለች።
የቻይና መንግሥት አገሪቱን በኮቪድ አያያዝ ዙርያ እየተቹ ናቸው ያላቸውን አንድ ሺህ የማኀበራዊ ሚዲያ ገጾችን ዘግቷል።
በአሁኑ ሰዓት በቻይና የተህዋሲው መስፋፋት ያሳሰባቸው ዩኬ፣ አሜሪካና ካናዳን ጨምሮ በርካታ አገራት ከቻይና የሚመጡ መንገደⶉች ላይ ከተህዋሲው ነጻ መሆናቸውን የሚመሰክር ሰርተፍኬት እንዲያመጡ እየጠየቁ ነው።