የክሪስ ሱቶን የወራጅ ቀጠና ፍልሚያዎች እና የካራባዎ ዋንጫ ግምት

ካሰሚሮ እና ጉማሬሽ
የምስሉ መግለጫ, ማንችስተር ዩናይትድ እና ኒውካስል በካራባኦ ዋንጫ ፍጻሜ እሁድ ይገናኛሉ።
ታትሟል

የሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ወሳኝ 25ኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች እና የካራባዎ ዋንጫ ፍልሚያን ያስተናግዳሉ።

የዚህ ሳምንት ዋነኛ ተኩረት በወራጅ ቀጠና ባሉ ቡድኖች መካከል የሚደረገው ፉክክር ነው።

በደረጃ ሰንጠረዡ በመጨረሻዎቹ 9 ክለቦች መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት 8 ብቻ ነው። ታዲያ ከእኒዘህ 9 ቡድኖች አራቱ እርስ በእርስ መገናኘታቸው በደረጃ ሰጠረዡ ግርጌ ላይ ለውጥ የመፍጠር ዕድሉ ሰፊ ነው።

የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱቶን የጨዋታ ግምቶቹን እንደሚከተለው አቅርቧል።

አርብ

ፉልሃም ከ ዎልቭስ

ሱቶን ባለፈው ሳምንት በአስደናቂ ሁኔታ ከሜዳቸው ውጪ ብራይተንን ማሸነፍ የቻሉት ፉልሃሞች ዎልቭስን ማሸነፍ አይሳናቸውም ይላል።

በፕሪሚየር ሊግ ሰንጠረዡ በአውሮፓ መድረክ ተሳታፊ መሆን የሚያስችል ደረጃ ላይ የሚገኙት ፉልሃሞች ያለ አጥቂያቸው አሌክሳንደር ሚትሮቪች ወደ ሜዳ ቢገቡም በደጋፊዎቻቸው ታጅበው ይህን ጨዋታ ያሸንፋሉ ብሏል።

ግምት፡ ፉልሃም 1 - 0 ዎልቭስ፤ ነገር ግን አርብ ምሽት የተደረገው ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ቀይ መስመር

ቅዳሜ

ኤቨርተን ከ አስተን ቪላ

ኤቨርተን ከወራጅ ቀጠናው ርቀው የሚገኙት በአንድ ነጥብ ልዩነት ብቻ ነው።

ለሾን ዳይሽ በሜዳው መጫወት የሰመረለት ይመስላል። ኤቨርተንን ከተረከበ በኋላ ያደረጋቸውን ሁለት ጨዋታዎች ማሸነፍ ችሏል። ከፕሪሚየር ሊጉ ላለመውረድ እየታገሉ የሚገኙ ኤቨርተኖች ለቪላ የሚመለሱ አይሆንም።

ቪላዎችም ቢሆኑ በየትኛው ደቂቃ ጎል የማስቆጠር አቅም አላቸው። ሁለቱም ክለቦች ጎል ሊያስቆጥሩ ይችላሉ ግን የሚሸናነፉ አይመስለኝም ይላል ሱቶን።

ግምት፡ ኤቨርተን 1 - 1 አስተን ቪላ

ሊድስ ከ ሳዝውሃምፕተን

ሊድስ ከ ሳዝውሃምፕተን

አንዱ የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ይህ ነው። የፕሪሚየር ሊጉ ግርጌ ላይ ተቀምጠው የሚገኙት ሳውዝሃምፕተን እና ሊድስ ናቸው።

ሳውዝሃምፕተኖች ባለፈው ሳምንት በሳታንፎርድ ብሪጅ ቼልሲ ላይ ያልተጠበቀ አስደናቂ ድልን ቢቀዳጁም ይህ ድላቸው የሊድስን ጨዋታ ቀላል አያደርግላቸውም ይላል ሱቶን።

ሊድሶች ወጥ የሆነ አቋም ማሳየት ተስኗቸዋል የሚለው ሶቶን፤ ምንም እንኳ ብዙ እምነት ባይኖረኝም ሊድሶች በደጋፊዎቻቸው ታጅበው ይህን ጨዋታ ሊያሸንፉ ይችላሉ ይላል።

ግምት፡ ሊድስ 2 - 1 ሳዝውሃምፕተን

ሌስተር ከ አርሰናል
የምስሉ መግለጫ, ሌስተር ከ አርሰናል

ሌስተር ከ አርሰናል

ሌስተሮች የያዙትን ስብስብ ከግምት በማስገባት ያሉበትን የደረጃ ሰንጠረዡ ስመለከት ያስደንቀኛል የሚለው ሱቶን፤ የቀበሮዎቹ ዋነኛ ችግር የተከላከያ መስመራቸው ነው ይላል።

ሱቶን በዚህም ብዙ ጎሎች ሊቆጠሩ እንደሚችሉ ግምቱን አስቀምጧል።

ሱቶን ባለፈው ሳምነት በነበራቸው ጨዋታ መድፈኞቹ ሁለት ጊዜ ከመመራት ተነስተው ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘው የወጡበት ሁኔታ በጣም አስደንቆኛል ያለ ሲሆን፤ አርሰናል ሌስተርን ያሸንፋል ሲል ግምቱን ሰጥቷል።

ግምት፡ ሌስተር 1 - 3 አርሰናል

ቀይ መስመር

ዌስት ሃም ከ ኖቲንግሃም ፎረስት

ዌስት ሃም በለንደን ስታዲየም ፎረስትን ማሸነፍ የማይችል ከሆነ ነገሮች ለዴቪድ ሞዬስ ጥሩ አይሆኑም።

ከዌስት ሃም በአምስት ነጥብ በአምስት ደረጃ ከፍ ብለው የሚገኙት ፎረስቶ ዌስት ሃምን መገዳደራቸው አይቀሬ ነው።

ግምት፡ ዌስት ሃም 1 - 1 ኖቲንግሃም ፎረስት

በርንዝማውዝ ከ ማንችስተር ሲቲ

በርንዝማውዝ ከ ማንችስተር ሲቲ

ሲቲዎች ከሜዳቸው ውጪ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ጥሩ አልነበሩም። ከፎረስት እና ከሊፕዚግ ጋር አቻ ተለያይተዋል።

ሲቲ ነጥብ መጣል የሚችልበት ሁኔታ ውስጥ አይደለም። ሱቶን ከዚህ ጨዋታ ለሲቲ ሦስት ነጥብ መሰብሰቡ ግድ ነው ይላል።

ግምት፡ በርንዝማውዝ 1 - 4 ማንችሰተር ሲቲ

ቀይ መስመር

ክርስታል ፓላስ ከ ሊቨርፑል

በቻምፒየንስ ሊጉ ሊቨርፑል 2 ለ 0 ሲመራ ከቆየ በኋላ በሪያል ማድሪድ 5 ለ 2 መሸነፉ የሳምንቱ ትልቁ መነጋገሪያ ጉዳይ ሆኖ ቆይቶ ነበር።

ሱቶን እንደሚለው በዚያ ምሸት የታየው ነገር የሊቨርፑልን ወቅታዊ ሁኔታ የሚያሳይ ነው ይላል።

ክሎፕ ጫናው እንዳይበረታባቸው ይህን ጨዋታ ማሸነፋቸው ግድ ቢሆንም፣ ይህ ጨዋታ ግን በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል ይላል።

ግምት ክርስታል ፓላስ 1 - 1 ሊቨርፑል

እሁድ

ቶተነሃም ከ ቼልሲ

ቶተነሃም ከ ቼልሲ

ሱቶን ይህን ጨዋታ ቼልሲ ያሸንፋል ይላል። ለዚህም ምክንያቱ በሊጉ ቼልሲ በቶተነሃም ላይ ያስመዘገበው ክብረ ወሰን ነው።

ቼልሲ በፕሪሚየር ሊጉ ከየትኛውም ክለብ በላይ ቶተነሃምን አሸንፏል። ከዚህ ቀደም በነበሩ ጨዋታዎች ከ24 ነጥብ 20 ነጥብ መሰብሰብ ችሏል።

ሱቶን ቼልሲ ሊያሸንፍ ይችላል የሚልበት ምክንያት ይህ ብቻ አይደለም። ከፍተኛ ጫና ውስጥ የሚገኙት ግራሃም ፖተር ይህን ጨዋታ ማሸነፋቸው ግድ ይላቸዋል።

ግምት፡ ቶተነሃም 1 - 2 ቼልሲ

ማንችስተር ዩናይትድ ከ ኒውካስል

ማንችስተር ዩናይትድ ከ ኒውካስል ዩናይትድ (የካራባዎ ፍጻሜ)

እሁድ ምሽት 1፡30 ሲል የዋንጫ ጨዋታ ይደረጋል። ማንችስተር ዩናይትድ ከ ኒውካስል ዩናይትድ በካራባዎ የዋንጫ ጨዋታ ተፋጠዋል።

ዩናይትድ አስደናቂ አቋም ላይ ይገኛል የሚለው ሱቶን፣ ለአሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ክብር እንዳለውም ይገልጻል። ይሁን እንጂ ቴን ሃግ እና ቡድናቸው እሁድ በዌምብሌ በኒውካስል ይፈተናሉ ይላል።

ኒውካስሎች ኒክ ፖፕን በቅጣት ስለሚያጡ በሦስተኛው ግብ ጠባቂ ካሪየስ ወደ ሜዳ መግባታቸው ለዩናይትድ እንደ መልካም አጋጣሚ የሚመለከቱ አሉ።

ካሪያስ የሊቨርፑል ግብ ጠባቂ ሳለ በሠራቸው ስህተቶች የቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ክለቡን አሳጥቷል ተብሎ ይወቀሳል። ሱቶን ግን ይህን ጨዋታ ካሪያስ ያን ስህተቱን የሚበቀልበት ዕድል ነው ይላል።

ግምት፡ ጨዋታው 1 አቻ ተጠናቆ ከተጨማሪ ሰዓት በኋላ፣ ኒውካስል ዩናይትድ በመለያ ምት ዋንጫውን ያነሳል ብሏል።