ቻይና የስራ አጥ ወጣቶችን አኃዝ ማተም ማቆሟ የምጣኔ ኃብቷ መቀዛቀዝ ማሳያ ነው ተባለ

ቻይናዊ ወጣቶች

የፎቶው ባለመብት, EPA-EFR/REX/Shutterstock

ታትሟል

ቻይና የስራ አጥ ወጣቶችን አሃዝ ማተም ማቆሟ ለአገሪቷ የምጣኔ ኃብት መቀዛቀዝ ቁልፍ ማሳያ ነው ተባለ።

ውሳኔው በዓለም ሁለተኛዋ ትልቅ የምጣኔ ኃብት በሆነውና በህብረተሰቡ ላይ በመጡ ለውጦች ምክንያት ነው ብለዋል የመንግሥት ቃለ አቀባይ።

በሰኔ ወር ከ16 እስከ 24 ዓመት በሆኑ በከተማ ነዋሪ ወጣቶች የታየው የስራ አጥነት 20 በመቶ በላይ በመሆን ከፍተኛ ጭማሬ ማሳየቱም ተነግሯል።

የቻይና ማዕከላዊ ባንክም የአገሪቱን ዕድገት እንዲያግዝ በማሰብ መበደርን የሚገታ ፖሊሲን አሳልፏል።

በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ የወጡ ይፋዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩ በሐምሌ ወር አጠቃላይ የቻይና የስራ አጥ አኃዝ ወደ 5.3 በመቶ ከፍ ብሏል።

መንግሥት የወጣቶች የስራ አጥ አኃዝ ለጊዜው ይፋ ማድረግ እንደሚያቆም ቢናገርም እስከመቼ እንደሚቆይ ግን የጊዜ ገደብ አልተሰጠም።

የአገሪቱ የብሔራዊ ስታቲስቲክስ ቢሮ ቃለ አቀባይ በበኩላቸው በወጣቶች ያለውን የስራ አጥ አኃዝ የማስላት ዘዴ እንደገና ሊጤን እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

“ምጣኔ ኃብቱ እና ህብረተሰቡ በየጊዜው እያደጉ እና እየተለወጡ ነው። የስታቲስቲክ ስራም እንደዛው በቀጣይነት መሻሻል እና መለወጥ ያስፈልገዋል” ሲሉም ፉ ሊንጊ በቤጂንግ በነበረ የዜና መግለጫ ተናግረዋል።

ከ16 እስከ 24 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ የተማሪዎች ቁጥር ማደጉ በስራ አጥ አኃዝ ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን ቃለ አቀባዩ ፍንጭ ሰጥተዋል። ቻይና በትምህርት ላይ ያሉ ወጣቶችን በስራ አጥ ቁጥሯ አታካትትም።

ቻይና የወጣቶችን የስራ አጥ አኃዝ ማተም የጀመረችው በጎሮጎሳውያኑ 2018 ነው። በአሁኑ ወቅትም በገጠር ያለውን የወጣቶችን የስራ ስምሪት ሁኔታም ላይ መረጃ አልሰጠችም።

የወጣቶች የስራ አጥ አኃዘም መታተም መቆምን ተከትሎ በቻይና ማህበራዊ ሚዲያ ዌይቦ ላይ መነጋገሪያ ሆኗል።

“አፍን በመሸፈን እና ዓይን በመጨፈር በእርግጥ ችግሮች ይፈታሉ?” እኔ እስካላሳወቅኩ ድረስ ማንም ሰው ስራ አጥ አይደለም ማለት ነው” ሲልም አንድ ግለሰብ ጠይቋል።

ቻይና የምጣኔ ኃብት እድገቷንም ለማገዝ የቻይና ማዕከላዊ ባንክ ባልተጠበቀ ሁኔታ የወለድ ምጣኔን ቀንሷል። ይህም በሶስት ወራት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገ ነው።

ባለፈው ሳምንት ቻይና የወጪ ንግዷ በከፍተኛ ሁኔታ ማሸቆልቆሉንም ሪፖርት አድርጋለች።

“በፖሊሲ ድጋፍ በቅርቡ ካልተሻሻለ በስተቀል ኢኮኖሚው ወደ ማሽቆልቆል ለመሄዱ እውነተና ስጋት አለ” ሲሉም የምጣኔ ኃብት የምርምር ማዕከል የሆነው ካፒታል ኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት ጁሊያን ኢቫንስ ፕሪቻርድ ለባለሃብቶች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።