ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዓለም ዋንጫ አስተናጋጅ ኳታር ከምድብ ጨዋታ ባሻገር መሄድ ሳትችል መሰናበቷ ተረጋገጠ
ኳታር ከሴኔጋል ጋር በነበራት ጨዋታ በገጠማት ሽንፈት ሳቢያ እያስተናገደችው ካለው የዓለም ዋንጫ ውድድር ከምድብ ጨዋታው ባሻገር ሳትሄድ መሰናበት የግድ ሆኖባታል።
ኳታር በውድድሩ የመክፈቻ ዕለት ከኢኳዶር ጋር በነበራት ጨዋታ ሁለት ለዜሮ በሆነ ውጤት ተሸንፋ ነበር ውድድሩን የጀመረችው፣ ትናንት አርብ ደግሞ ከአፍሪካዊቷ ሴኔጋል ጋር ገጥማ 3 ለ 1 በሆነ ውጤት ተረትታለች።
በዚህም ሳቢያ ኳታር ማድረግ ካለባት ሦስት የምድብ ግጥሚያዎች ሁለቱን በመሸነፏ ወደ ቀጣይ ዙር የማለፍ እድሏን በሌሎች ቡድኖች ጨዋታ ላይ የተንጠለጠለ አድርጎት ነበር።
ነገር ግን የምድኑ ኃያላን ኢኳዶር እና ኔዘርላንድ ነጥብ ተጋርተው በመውጣታቸው ኳታር የሚቀራትን የመጨረሻ ጨዋታ አድርጋ ውጤቱ ምንም ቢሆን ከውድድሩ ለመሰናበት ተገዳለች።
ኳታር የምድብ ጨዋታ መረሃ ግብሯን ብቻ ለማሟላት የአውሮፓ የእግር ኳስ አንጋፋ ከሆነችው መካከል አንዷ ከሆነችው ከኔዘርላንድስ ጋር በሚቀጥለው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዋን አድርጋ ትሰናበታለች።
ኳታር በሴኔጋል ከተሸነፈች በኋላ በውድድሩ ውስጥ ለመቆየት በመጀመሪያ ጨዋታዋ ካሸነፈቻች ኢኳዶር አስቸጋሪ ውለታን ማግኘት ነበረባት።
ነገር ግን ከኔዘርላንድ ጋር የገጠመችው የደቡብ አሜሪካዋ አገር ኢኳዶር አንድ አቻ በመውጣቷ፣ ኳታር ከምድብ ውድድሩ ለመሻገር ሳትችል ቀርታለች።
በዚህ ምድብ በመጀመሪያ ጨዋታቸው በኔዘርላንድስ 2 ለ 0 የተሸነፉት የአፍሪካ ሻምፒዮኖቹ ሴኔጋሎች፣ ከሽንፈታቸው አገግመው ኳታርን በማሸነፍ በምድብ ውድድሩ ውስጥ ተፎካካሪነታቸውን አጠናክረዋል።
ኳታር አረቡ ዓለም የመጀመሪያውን የዓለም ዋንጫን ከማስተናገዷ በተጨማሪ ብሔራዊ ቡድኗም በዓለም ዋንጫ ውድድር ሲሳተፍ የመጀመሪያው ነው።
ከውድድሩ የመክፈቻ ዕለት አንሰቶ ባሉት ስድስት ቀናት ውስጥ ሁለት ጨዋታዎችን ያደረገችው ኳታር፣ አምስት ግቦች ተቆጥረውባት አንድ ግብ አስቆጥራ በጨዋታዎቹ ተሸንፋለች።
ቀሪ ጨዋታዋን በመጪው ማክሰኞ ከኔዘርላንድስ ጋር የምታደርግ ሲሆን፣ ቀላል ይሆንላታል ተብሎ አይጠበቅም።
ኳታር ቢሊዮኖችን አፍስሳ ዘመናዊ ስታዲየሞችን በመገንባት ለአረቡ ዓለም የመጀመሪያ የሆነውን ዓለም አቀፉን እግር ኳስ ውድድር በማስተናገድ ታሪክ አስምዝገባለች።
ነገር ግን በውድድሩ ላይ ብሔራዊ ቡድኗ በተከታታይ ጨዋታዎቹ ሽንፈት ስለገጠመው በዙር ውድድሩ ላይ በመሰናበቷ ከሆነ፣ የዓለም ዋንጫን አስተናግዳ በምድብ ጨዋታ ከውድድሩ ውጪ በመሆን ከደቡብ አፍሪካ ቀጥላ ሁለተኛዋ አገር ሆናለች።
ከሁለት ጨዋታዎች ተመሳሳይ አራት ነጥብና ሁለት የግብ ልዩነቶች ይዘው የምድቡን የመሪነት ስፍራ የያዙት ኢኳዶር እና ኔዘርላንድስ በአንደኝነት ወደ ቀጣይ የጥሎ ማለፍ ውድድር ለመግባት ተጋጣሚዎቻቸውን ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል።
በዚህም መሠረት በአውሮፓ ሊጎች ውስጥ በሚሰለፉ ተጫዋቾች ከተገነባችው ሴኔጋል ጋር የምትገጥመው ኢኳዶር ከባድ ፈተና የሚጠብቃት ሲሆን፣ ከወዲሁ ከውድድሩ መውጣቷን ካረጋገጠችው ከኳታር ጋር የምትገጥመው ኔዘርላንድስ ግን በአሸናፊነት የምድቡን የበላይነት ትይዛለች ተብሎ ይጠበቃል።