ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ ወደ አሜሪካ ሲበሩ ሉላ የብራዚል ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሃላ ፈፀሙ
ሊዩዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ የብራዚል ፕሬዚደንት ሆነው ቃለ መሃላ ፈጸሙ።
ሉላ በአገሪቷ ከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ሲቀመጡ ይህ ሦስተኛ ጊዜያቸው ነው።
ሉላ በሚለው ስማቸው በስፋት የሚታወቁት ግራ ዘመሙ ፖለቲከኛው እንደ አውሮፓውያኑ በ2003 እና 2010 መካከል ባሉት ዓመታት አገሪቷን መርተዋል።
አሁን ደግሞ ሉላ ጥቅምት ላይ በተካሄደው ምርጫም ጄር ቦልሶናሮን አሸንፈው የፕሬዝዳንትነት መንበሩን ይዘዋል።
ሉላ መጀመሪያ ላይ ባደረጉት ንግግር በመፈራረስ ላይ ያለችውን አገር መልሶ ለመገንባት ቃል የገቡ ሲሆን የርክክብ ሥነ ሥርዓቱን ላለመፈፀም አርብ ዕለት ወደ አሜሪካ የሄዱት የቀድሞው መሪ ፖሊሲዎችንም ተቃውመዋል።
የሉላ ደጋፊዎች ከጠዋት ጀምሮ በምክር ቤቱ ፊት ለፊት የተሰባሰቡት የሠራተኛ ፓርቲን ቀለም ያለው አርማ ይዘው ነበር።
ደጋፊዎቻቸው ወደ ምክር ቤቱ ያመሩት መሪያቸው የሚፈፅሙትን ቃለ መሃላ ሲፈፅሙ ለማየት ብቻም ሳይሆን ለማክበርም ጭምር ነው።
ታዋቂውን የሳምባ አርቲስት ማርቲነሆ ዳ ቪላን ጨምሮ ከ60 የሚበልጡ አርቲስቶች ‘ሉላፓሎዛ’ የሚል ስያሜ በተሰጠው የሙዚቃ ዝግጅት ላይ በብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ባሸበረቁ ሁለት ግዙፍ መድረኮች ላይ ለመጫዎትም ቀጠሮ ይዘው ነበር።
ከፕሬዝዳንቱ የትውልድ ሥፍራ ፐርናማቡኮ የመጣችው ጁሊያና ባሬቶ አገሯ ቀደም ብላ አደጋ ላይ እንደነበረች ለቢቢሲ ተናግራለች።
አንድ ግለሰብም “ፍቅር ጥላቻን አሸንፏል” የሚል ባነር ይዟል።
ሌላኛዋ በሙዚቃ ዝግጅቱ ላይ ለመታደም የተሰለፈች የፕሬዚደንቱ ደጋፊ ደግሞ “ብራዚል ይህ ለውጥ ያስፈልጋታል” የሚል ጽሑፍ ይዛ ታይታለች።
ሉላ እና ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጄራልዶ አልክሚን ቃለ መሃላ የፈፀሙት በመደበኛው በዓለ ሲመት ሥነ ሥርዓት መጀመሪያ ላይ ነበር።
ተመራጮቹ ያለፉትን ቀናት ካቢኔያቸውን በመምረጥ እና ደጋፊዎቻቸውን ወሳኝ በሆኑ የመንግሥት ሥልጣን ላይ በመሾም ነበር።
ቃለ መሃላውን ከፈፀሙ በኋላም ሉላ በብራዚል ሕዝብ ላይ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸው፤ አገሪቷን ለመገንባት እንዲሁም የሁሉም የሆነችውን ብራዚልን ለመፍጠር ቃል ገብተዋል።
ሉላ በምክር ቤቱ ያደረጉት አብዛኛው ንግግር ስለ አንድነት እና መልሶ ግንባታ ላይ ያተኮረ ነበር።
እነዚህ ቃላትም ለተከፋፈለችው፣ በወረርሽኝና ጽንፍ በረገጠ ፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ለገባችው ብራዚል ወሳኝ ናቸው ተብሏል።
ሉላ ለትምህርት፣ ለጤና እና ለአማዞን ደን ጥበቃ ላይ የነበረውን የቀድሞው ፕሬዝዳንት ራዕይን ለመቀልበስም ቃል ገብተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ አወዛጋቢ የሆነውን የቦልሶናሮን የጦር መሣሪያ ሕግ አነሳለሁ ብለዋል።
ሉላ መንግሥታቸው ለበቀል እንደማይነሳሳ ገልጸው ስህተት የሰሩት ግን ለስህተታቸው መልስ ያገኛሉ ብለዋል።
ከእነዚህ መካከል የቦልሶናሮ ኮቪድ 19 ፖሊሲ በመጥቀስም የቀድሞ ፕሬዝዳንቱ "የዘር መጥፋት" እንዲደርስ ምክንያት ሆነዋል ሲሉ ከሰዋቸዋል።
አዲሱ ፕሬዝዳንት በሌላ ንግግራቸው በቦልሶናሮ አስተዳደር የብራዚል የአየር ንብረት ለውጥ አክቲቪስት የነበረችው ማሪና ሲልቫ ለአካባቢ እና ለአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ኃላፊ ሆና መሾሟን ገልጸዋል።
ሉላ በአውሮፓውያኑ 2030 ለማሳካት ቃል የገቡትን ‘ዜሮ ዲፎሬስቴሽንን ‘ ምንም ዓይነት የደን ጭፍጨፋ እንዳይኖር የማድረጉን ዓላማ ታሳካለች ተብሎም ይጠበቃል።
ይሁን እንጂ አሁንም ከቀድሞው ፕሬዚደንት ደጋፊዎች ተቃውሞን እያስተናገዱ ነው።
የብራዚል መንግሥት በቀድሞው ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ ደጋፊዎች ብጥብጥ ሊፈጥሩ ይችላሉ በሚል ስጋት ስምንት ሺህ የሚጠጉ የፖሊስ መኮንኖችን በከተማዋ አሰማርቷል።
እሁድ ዕለት አንድ ግለሰብ ስለት እና ተቀጣጣይ ርችት ይዞ ክብረ በዓሉ ወደ ተዘጋጀበት ቦታ ለመግባት ሲሞክር በቁጥጥር ሥር መዋሉን የብራዚል ፖሊስ አስታውቋል።
ባለፈው ሳምንትም ባለሥልጣናት በገና በዓል ዋዜማ ላይ በዋና መዲናዋ በሚገኝ አየር ማረፊያ አቅራቢያ የነዳጅ ታንከርን ለማቃጠል የሞከረ የቦልሶናሮ ደጋፊን አስረዋል።
ግለሰቡ ከሉላ በዓለ ሲመት ቀደም ብሎ ብጥብጥ ለመፍጠር አስቦ እንደነበር ተናግሯል።
ሌሎች የቀድሞው ፕሬዝዳንት ደጋፊዎችም ከጦሩ ዋና መሥሪያ ቤት ተሰባስበው የቆዩ ሲሆን መፈንቅለ መንግሥትም እንዲፈፀም ሲያነሳሱ ቆይተዋል። ፖሊስ እነዚህን ደጋፊዎች ሐሙስ ዕለት ለማስነሳት ሞክሮ ነበር፤ ነገር ግን በኃይል ምላሽ ከሰጡ በኋላ ጥለው ወጥተዋል።
ሆኖም ቦልሶናሮ በሽንፈታቸው ምክንያት የሚነሳን ተቃውሞ አውግዘዋል። ደጋፊዎቻቸውም ደንቦችና ሕገ መንግሥቱን በማክበር "ከሌላው የተለዩ" መሆናቸውን እንዲያሳዩ አሳስበዋል።