ምዕራባውያን ሩሲያውያን ጎብኚዎችን እንዲያግዱ ዩክሬን ጠየቀች

ታትሟል

ሩሲያ ዩክሬን ላይ ጥቃት ከከፈተች በኋላ በርከታ ማዕቅቦችን አስተናግዳለች። ሆኖም ከጦርነቱ በፊት እንደነበረው ሁሉ መደበኛ የሩሲያ ዜጎች አሁንም ድረስ አውሮፓን እና አሜሪካን መጎብኘት ይችላሉ።

ታዲያ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የምዕራባውያ መንግሥታት ማንኛውም የሩሲያ ዜጋ ሀገራችሁን እንዳይጎበኝ አግዱልኝ የሚል ጥሪ አቅርበዋል።

የቭላድሚር ፑቲን ቢሮ ክርሚሊን በበኩሉ ለዚህ ጥሪ ንቀት የተሞላበት ምላሽ ሰጥቷል።

ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ሩሲያውያን “ፍልስፍናቸውን እስኪቀይሩ ድረስ በራሳቸው ዓለም መኖር ይገባቸል” ሲሉ ለዋሽንግተን ፖስት ተናግረዋል።  

እንዲህ አይነት እገዳ መንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸውን የሩሲያ አየር መንገዶች አሁን ከጣለባቸው እገዳ በላይ ውጤታማ እንዲሆን ይረዳል ሲሉም አስረድተዋል።

ይህ የዜሌንስኪ ጥሪ ድጋፍ የማግኘት እድሉ የጠበበ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ሩሲያ ከማዕቀቡ ባሻገር በዓለም ዙሪያ በንግድ የተሳሰረች ስትሆን ሩሲያውያን ቱሪስቶች እንደ ግብጽ፣ ቱርክ እና የተባበሩት አርብ ኤሜሬት ባሉ ሀገራት በጥሩ ሁኔታ ይስተናገዳሉ።

የኢስቶኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ካጃ ካላሳ በትዊተር ገጻቸው ለሩሲያ ቱሪስቶች ቪዛ እንዳይሰጥ ጠይቀዋል።

ባለፈው ወር ደግሞ የላትቪያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ለሰብዓዊ ጉዳይ ከሚጓዙ በስተቀር የአውሮፓ ሀገራት ለሩሲያውን ቪዛ ከመስጠት መቆጠብ አለባቸው ብለው ነበር።

ከቀናት በፊት የሩሲያ ጎረቤት ፊላንድ የሩሲያ ጎብኚዎች ማገድን እደግፋለው ብላለች።

በቅርብ በአውሮፓ ህብረት በሚኖረው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ፊላንድ እና ኢስቶኒያ ጉዳዩን ለንግግር እንደሚያቀርቡት ይጠበቃል።

የቭላድሚር ፑቲን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ የዜሌንስኪን ሃሳብ ያወገዙ ሲሆን “ይህ ሊታይ የሚችለው በአሉታዊ ጎኑ ብቻ ነው” ብለዋል።

“ሩሲያውያንን ወይም ሩሲያን ለማግለል የሚደረግ ማንኛው ሙከራ ተስፋ ቢስ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።