“አለቃዬ በቢሯችን ያሉ ወንዶችን ፎጣ እንዳጥብ አዘዘኝ”

ዩና ከሰራችበት ባንክ ፊት ለፊት ሆና
የምስሉ መግለጫ, ዩና ከሰራችበት ባንክ ፊት ለፊት ሆና
ታትሟል

ዩና የባንክ ፀሐፊ ሆና በተቀጠረችበት የመጀመሪያው ቀን ያልጠበቀችው የሥራ ጫና ገጠማት።

ምሳ ሥሪ ከዚያም የወንዶች መጸዳጃ ያለውን ፎጣ ቤት ወስደሽ እጠቢ ተባለች። እነዚህ ሥራዎች የተሰጧት የባንኩ አዲስ ሴት ሠራተኛ በመሆኗ እንደሆነ ተነገራት።

ሥራዎቹን እንደማትቀበል ገለጸች። “ወንዶቹ የራሳቸውን ፎጣ ቤት ወስደው ለምን አያጥቡም?” ስትል ጠየቀች። አለቃዋ “እንዴት ወንዶች ልብስ ይጠቡ ትያለሽ” ሲል ተቆጣት።

ቅሬታ ማቅረቧ በበጎ አልተወሰደም። እሷም ፎጣዎቹን ታጥብ ጀመር።

ከሚደርስባት ትንኮሳ ባሻገር ሴት የሥራ ባልደረቦቿ ሊደግፏት አለመፍቀዳቸው አሳዘናት።

ባንኩ ያደረሰባትን በተንቀሳቃሽ ምሥል ቀርጻ ምርመራ እንዲደረግበት ለደቡብ ኮሪያ መንግሥት አስታወቀች።

የሥራ ባልደረቦቿ እንደሷው በ20ዎቹ ዕድሜ ክልል ቢሆኑም “ሁሉም መሥሪያ ቤት እንዲህ ነው” ብለው አጣጣሏት።

ደቡብ ኮርያ በቴክኖሎጂ እየበለጸገች ነው። ከዓለም ሀብታም አገራት አንዷ ለመሆን በምታደርገው ጉዞ ግን ሴቶች ተዘንግተዋል።

ሴቶች ከወንዶች ሦስት እጥፍ ያነሰ ነው ደመወዛቸው። ከሀብታም አገራት በወንዶች እና በሴቶች ደመወዝ መካከል ከፍተኛ ልዩነት ያለባት አገር ናት።

ወንዶች ፖለቲካውንም የቦርድ ስብሰባውንም ተቆጣጥረውታል።

ሴቶች ከሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ከፍተኛውን ሥልጣን የያዙት በ5.8 በመቶውን ብቻ ነው።

የቤት ሥራና ልጅን መንከባከብ ለሴቶች ብቻ ተትቷል። ወሲባዊ ጥቃትም ተንሰራፍቷል።

ቴክኖሎጂ የጎመራበት አገር እንደመሆኑ የበይነ መረብ ወሲብ-ነክ ወንጀሎች ተበራክተዋል።

ሴቶች መጸዳጃ ቤት ወይም ልብስ መቀየሪያ ክፍል ሳሉ በድብቅ ቀርጸው የሚለቀቁ ወንጀለኞች በዝተዋል።

ችግሮችን ለመፍታት ቃል ከመግባት ይልቅ የደቡብ ኮሪያ አዲሱ ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ-ዮል “መዋቅራዊ የፆታ መድልዎ የድሮ ችግር ነው” ሲሉ አጣጥለዋል።

እኩልነት እንዲሰፍን የሚደረግ ጥረትን ወንዶችን ‘ለመጨቆን’ የሚውል አድርገው የሚመለከቱ ወንዶች በፕሬዝዳንቱ ንግግር የልብ ልብ ተሰምቷቸዋል።

ሥልጣን ከያዙ በኋላ በመሥሪያ ቤቶች ያለውን ፆታን ያማከለ ቅጥር አንስተዋል። ቅጥር የሚፈጸመው በፆታ ሳይሆን በችሎታ ነው ሲሉም ተደምጠዋል።

ሆኖም ግን ከ19 የካቢኔ አባላቸው ሴቶች ሦስት ብቻ ናቸው።

ይባስ ብሎ የፆታ እኩልነት ሚኒስትርን ለማጠፍ እየሞከሩ ነው። መሥሪያ ቤቱ ሴቶች እና የወሲባዊ ጥቃት ሰለባዎችን የሚደግፍ ነው።

መሥሪያ ቤቱ እንዳይዘጋ ከ800 በላይ መሥሪያ ቤቶች በጥምረት ተቃውሞ አሰምተዋል።

የ28 ዓመቷ ፓርክ ጂ-ሀይን ከተቃዋሚዎቹ አንዷ ናት። የተቃዋሚ ፓርቲን እንድትመራ ተጠይቃ ነበር። የወጣት ሴቶችን ውክልና እንድታስጠብቅ የተሰጣትን የመሪነት ቦታ በስድስት ወር አጣችው።

የግድያ ዛቻ ስለሚደርሳትና የት እንደምትኖር መረጃው ይፋ ስለተደረገ ለመደበቅ ተገዳለች።

ፓርክ ጂ-ሀይን
የምስሉ መግለጫ, ፓርክ ጂ-ሀይን

በስድስቱ ወራት ውስጥ ፖለቲካው በወንዶች የበላይነት የተያዘ መሆኑን አይታለች። ስብሰባ ላይ ብቸኛዋ ሴት ትሆን ነበር።

ሐሳብ ስትሰጥ ችላ ይሏት ነበር።

“ስለ ምጣኔ ሀብት ወይም የአየር ንብረት ለውጥ ሳወራ ‘አንቺ እንኳን የሴቶች ጉዳይ እና ወሲብ-ነክ ጉዳዮች ላይ አተኩሪ’ ይሉኝ ነበር” ስትል ታስታውሳለች።

ኃላፊነቱን የሰጧት የሴቶችን ድምጽ ለማግኘት እንደሆነ ተረድታለች።

በበይነ መረብ የሚፈጸም ወሲብ-ነክ ወንጀልን ካጋለጠች በኋላ ነው ፓርክ ታዋቂ የጋዜጠኝነት ተማሪ የሆነችው።

ዘገባዋን ተከትሎ ወንጀለኞቹ ታስረዋል።

አምና 11,568 የበይነ መረብ ወሲብ-ነክ ወንጀሎች ሪፖርት ተደርገዋል። ካለፈው ዓመት 82 በመቶ ጨምሯል።

ድብቅ ካሜራዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ ብዙ ሴቶች የሕዝብ መጸዳጃ ለመጠቀም ይፈራሉ።

ቪድዮዎቹ ሴቶችን ገንዘብ ለመበዝበዝ ይውላሉ። ለሕዝብ ቪድዮዎቹን የሚለቁም አሉ።

ፓርክ በፓርቲዋ ውስጥ የሚሰሙ የወሲባዊ ትንኮሳ ክሶችን ለመመርመር ስትሞክር ‘ችግር ፈጣሪ’ ተብላ ከፓርቲው ተገፋች። ከፓርቲው ብትወጣም ባደረገችው ትግል ብዙ ሴቶች ያመሰግኗታል።

ተቃዋሚዎች

እአአ በ2018 በደቡብ ኮሪያ የሚቱ (#MeToo) ንቅናቄ ተካሂዷል። ከእስያ የመጀመሪያው እና ትልቁ የሚቱ እንቅስቃሴ ነው።

በተቃራኒው የፆታ እኩልነት ጥያቄን የሚያናንቅ ንቅናቄ ተጀመረ። ሴቶች ማኅበረሰባቸው ውስጥ የተሻለ ቦታ እየተሰጣቸው መሆኑን የሚቃወሙ ወንዶች ነበሩ።

ሴታዊነት (feminism) ጽዩፍ ቃል እንዲሆን ነበር የዚህ ንቅናቄ ዓላማ። በአገሪቱ አሁንም ድረስ የተወሰኑ ሴቶች ቃሉን እንዲፈሩት አድርጓል።

የፆታ እኩልነት ሚኒስቴር እንዲዘጋ ምክንያት የሆነው የ37 ዓመቱ ሊ ጁን-ሶክ “ሴቶች መብታቸውን ተገፈው ኖረዋል። የተለወጡ ነገሮች ግን አሉ” ይላል።

ፓርቲው ምርጫ እንዲያሸንፍ ከማድረጉም በላይ የወጣት ወንዶችን ድምጽ አግኝቷል።

“የፆታ እኩልነት አዲስ መልክ ይዟል። ከሴታዊነት ወጥቶ ለሁሉም ጭቁኖች መብት የሚታገል ሥርዓት ያስፈልጋል” ሲል ያክላል።

ከ20 ዓመት በፊት የተከፈተው መሥሪያ ቤቱ ከመንግሥት በጀት 0.2 በመቶ ቢመደብለትም ሴቶች ሕይወታቸውን እንደለወጠው ይናገራሉ።

በድብቅ ካሜራ የተቀረጹ ቪድዮዎች ሰለባ የሆኑ፣ በማርገዛቸው ከሥራ የተባረሩ እና ያለ አጋር ልጅ የሚያሳድጉ ሴቶችን ረድቷል።

አና መሥሪያ ቤቱ ሊዘጋ እንደሆነ ከሰማች ጀምሮ መተኛት አልቻለችም።

ከስድስት ዓመታት በፊት በኮሌጅ አስተማሪዋ ከተደፈረች በኋላ ማንም ከጎኗ ሊቆም ሳይፈቅድ፣ ይህ መሥሪያ ቤት ሕይወቷን እንዳዳነው ትናገራለች።

መደፈሯን ለአባቷ ደውላ ስትናገር ‘ቤተሰቡን አዋርደሻል’ ብለው ስልኩን እንደዘጉባት ታስታውሳለች። አና በምሥጢራዊ ማገገሚያ ማዕከል ውስጥ እየኖረች ነው።

አና
የምስሉ መግለጫ, አና
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አና ሚቱ ንቅናቄ ከተጀመረ በኋላ ነው ብርታት አግኝታ እርዳታ የጠየቀቸው።

ወንጀሉን ለመጠቆም ስትሞክር የሐኪም ማስረጃ አምጪ ተባለች። ሐኪሞች ግን ‘ቅዠታም ነሽ’ ብለው መለሷት።

“ልብ የሚሰብር ነበር። የእርዳታ ማዕከል ያለው ሐኪም እንዴት አልተባበርም እንደሚል አልገባኝም። መውጫ የሌለው ጨለማ ክፍል ውስጥ እንደተዘጋብኝ ተሰማኝ” ስትል ወቅቱን ታስታውሳለች።

ከወራት በኋላ ራሷን ለማጥፋት ሞከረች።

የፆታ እኩልነት ሚኒስቴር ደኅንነቱን የጠበቀ መኖሪያ አግኝቶላት የሥነ ልቦና ድጋፍ እየተሰጣት ቆየ።

የደፈራት አስተማሪ እስራት ተፈርዶበታል።

“ከገዛ ቤተሰቤ በላይ ይህ መሥሪያ ቤት ረድቶኛል። መሥሪያ ቤቱን መዝጋት መጥፎ ሐሳብ ነው” ትላለች።

የፆታ ሚኒስቴር የሚሰጣቸው አገልግሎቶች በሌላ መሥሪያ ቤት ሥር እንደሚሰጡ መንግሥት ገልጿል።

ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት አዲሱ አስተዳደር ለሴቶች “የተሻለ ከለላ ይሆናል።” ይህንን ያሉበት ምክንያት ግልጽ አይደለም።

የመንግሥት ዕቅድ በምክር ቤት አብላጫ ድምጽ ያላቸው ተቃዋሚዎች ሊያፈርሱት ይችላሉ።

መሥሪያ ቤቱ መዘጋቱ ሴቶች በቤት እና በሥራ ቦታ የሚገጥማቸውን መሰናክል እንደሚጨምር የገለጹ አሉ።

በደቡብ ኮሪያ ቤቶች ከወለዱ በኋላ ወደ ሥራው ዓለም ለመመለስ ይቸገራሉ።

የ50 ዓመቷ ሺል ሁዮን-ዩንግ የትምህርት ቤት አስተዳዳሪ ነበረች። ትምህር ቤቱ ቅዳሜ እንድትሠራ ሲጠይቃት ልጇን የሚጠብቅላት አልነበረም። ባለቤቷም ልጃቸውን ለመያዝ ስላልፈቀደ ከሥራ ለመልቀቅ ተገደደች።

“ባለቤቴ የአባታዊ ሥርዓት የተጫነው ወንድ ነው። ምንም አያግዘኝም” ትላለች።

መንግሥት ያወጣው አሃዝ እንደሚያሳየው 46 በመቶ ሴት ሠራተኞች ቋሚ የሥራ ኮንትራት የላቸውም። ይህ ቁጥር በወንዶች ዘንድ ብቻ 30 በመቶ ነው።

ሺል ሁዮን-ዩንግ
የምስሉ መግለጫ, ሺል ሁዮን-ዩንግ

ሺል በጽዳት ሥራ ነው እየተዳደረች ያለችው። ከእሷ ጋር የሚሠሩ ሁለት በ30ዎቹ ዕድሜ ክልል ያሉ ሴቶች ወደዚህ ሥራ የገቡት ልክ እንደሷው በቀድሞ ሥራቸው እንዳይዘልቁ በመደረጋቸው ነው።

ሥራቸውን ማጣት የማይፈልጉ ሴቶች ልጅ ላለመውለድ እየወሰኑ ነው።

የአገሪቱ የወሊድ መጠን ወደ 0.81 በመቶ አሽቆልቁሏል። ይህም ከዓለም አነስተኛው ነው። በምዕተ ዓመቱ መጨረሻ የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት የሚያሳልጥ በቂ የሥራ ኃይል ላይኖርም ይችላል።

ለአንድ ዓመት የፆታ እኩልነት ሚኒስቴርን የመሩት ጄንግ ሁይን-ቤይክ እንደምትለው፣ የፆታ እኩልነት ካልሰፈነ የወሊድ መጠን ሊጨምር አይችልም።

ሚቱ ወሲባዊ ጥቃትን በተመለከተ ንቅናቄ በመፍጠር ለውጥ ቢያመጣም የሴቶችን የሥራ ዕድል እና ተከፋይነት በማረጋገጥ ረገድ መዋቅራዊ ለውጥ እንደሚያሻ ትናገራለች።

ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ-ዮል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ-ዮል

አሁን ላይ የአገሪቱ የፆታ እኩልነት ሚኒስቴር የሆኑት ኪም ሁያን-ሱክን ለማነጋገር ቢቢሲ ለወራት ያደረገው ጥረት ባይሳካም አንድ መሰናዶ ላይ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ “በፖለቲካው ብዙ ሴቶች ያስፈልጋሉ። በተለይም በአመራር ሴቶች ሲኖሩ በወንዶች እና ሴቶች መካከል ያለው የደመወዝ እና ኮንትራት ልዩነት ይቀረፋል” ሲሉ መልሰዋል።

የዚህ ዘገባ መነሻ ላይ የተጠቀሰችው ዩና ባለፈው ወር ከመንግሥት በደረሳት የስልክ ጥሪ፣ የምትሠራበት ባንክ ሕግ መጣሱ ተነግሯታል።

በባንኩ ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰና መድልዎም እንደተፈጸመ በመግለጽ ባንኩ ቅጣት እንዲከፍል፣ ዩናም ወደ ሌላ ቅርንጫፍ እንድትዛወር ተወስኗል።

የእሷን ክስ ተከትሎ ሌሎችም ሴት ሠራተኞች ቅሬታቸውን ለማሰማት ድፍረት አግኝተዋል። ሆኖም ግን የፆታ እኩልነት ሚኒስቴር ከፈረሰ የታየው ጭላንጭል ተስፋ እንደሚከስም ዩና ትናገራለች።