ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቅዱስ ሲኖዶስ የትግራይ አባቶችን አውግዞ ሲለይ፣ የትግራይ አባቶች ተቃወሙ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በቅርቡ በአክሱም ጽዮን ማርያም የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት የሰጡ እና የተቀበሉ የትግራይ አባቶችን አውግዞ ከቤተ ክርስቲያኗ የተሰጣቸው የክህነት ሥልጣን ተሽሮ እንዲለዩ መወሰኑን አስታወቀ።
ቅዱስ ሲኖዶሱ ረቡዕ ሐምሌ 26/ 2015 ዓ.ም. ያደረገውን አስቸኳይ ምልዓተ ጉባኤን ተከትሎ ባስተላለፈው ውሳኔ የትግራይ ቤተ ክህነት ያደረገችው የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት “ሕገወጥ እና የቤተክርስቲያኗን ዶግማ፣ ቀኖና እና የአስተዳዳራዊ ጥሰትን” የፈጸመ ነው ብሏል።
ይህንን ውግዘት ተከትሎ የትግራይ ሐሙስ ሐምሌ 27/2015 ዓ.ም. የትግራይ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ውግዘቱ ተቀባይነት የሌለው ነው ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።
የቤተ ክርስቲያኗን ቀኖናን ከመጣስ በተጨማሪ “አንዲት፣ ዓለም አቀፋዊት የሆነችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የሚከፋፍል፣ የአገር አንድነትን የሚሸረሽር እና የሚያፈርስ፣ ምዕመናንን ከምዕመናን ጋር የሚያጋጭ እና ሰላምን የሚያናጋ ነው” ሲል ቅዱስ ሲኖዶሱ ባወጣው መግለጫ ላይ አስፍሯል።
ቅዱስ ሲኖዶስ ይህንን ውሳኔ ያስተላላፈው የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ሰላማ ቤተ ክህነት ከተመረጡት አስር ኤጲስ ቆጳሳት መካከል የዘጠኙን ሲመት ባለፉት ሳምንታት በአክሱም ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ማከናወኑን ማሳወቁን ተከትሎ ነው።
በትግራይ የተቀሰቀውን ጦርነት ተከትሎ የትግራይ ቤተ ክህነት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሲኖዶስ ጋር ያለውን ግንኙነት በማቋረጥ መንበረ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ቤተ ክህነትን መመስረቱን ማስታወቁ ይታወሳል።
ቅዱስ ሲኖዶሱ ሲመቱንም አስመልክቶ በቤተ ክርስቲያኗ ሕግ እና ቀኖና መሠረት የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ እና ሥልጣን የመወሰን የቅዱስ ሲኖዶስ መሆኑን የሚጥስ፣ የቅዱስ ፓትርያርኩን የማዕረግ ስም እና መንበር የሚያፋልስ መሆኑንም አትቷል።
ይህንንም በመመርኮዝ የቤተ ክርስቲያኗን ሃይማኖታዊ ሕግጋት እና ቀኖናን የሚያፋልስ ሊቀ ጳጳስ/ኤጲስ ቆጶስ ከአባልነት እንደሚሰረዝ በመደንገጉ ቅዱስ ሲኖዶሱ አባቶቹን አውግዞ መለየቱን አስታውቋል።
በዚህም መሠረት ከዲቁና ጀምሮ ያለው ሙሉ የክህነት ሥልጣን ተሽሮም በቀድሞ ዓለማዊ ስማቸው እንዲጠሩ በቤተ ክርስቲያኗ መንፈሳዊ አገልግሎት ዙርያም በሕይወትም ሆነ በሞት ማናቸውንም አገልግሎት እንዳያገኙም መወሰኑን አስታውቋል።
ይህም ውሳኔ የኤጲስ ቆሳት ሹመትን የሰጡትን የትግራይ ሊቀ ጳጳሳትን አባ ኢሳይያስ፣ አባ መርቃርዮስ፣ አባ መርሃ ክርስቶስ፣ አባ ጴጥሮስን መንበረ ሰላማ ብሎ “ሕገወጥ መንበር” በመሰየም እና ቀኖና እና ሥርዓትን በጣሰ መልኩ ሹመት በመስጠት ተወግዘው መለያታቸውን አስፍሯል።
ነገር ግን በትግራይ ያሉ የቤተክርስቲያኗ አባቶች የተለለፈባቸውን ውግዘት እና እገዳን ውድቅ በማድረግ በውሳኔያቸው እንደሚገፉበት እና ውግዘቱ ምንም አይነት ተጽእኖ እንደሌለው ገልጸዋል።
አባቶቹ ጨምረውም ወደፊት ሊኖር ለሚችለው መልካም ግንኙነት ሲባል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ያስተላለፈውን ውሳኔ መልሶ እንዲያጤነው ጠይቀው፣ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን የበኩላቸውን እርምጃ እንደሚወስዱ አሳውቀዋል።
ቅዱስ ሲኖዶሱ “ከጥንት ጀምሮ መንበር ያለ ፓትርያርክ የማይሰየም በመሆኑም የፓትርያርኩን እና የሲኖዶሱን ሥልጣን ተቃውመዋል፤ እንዲሁም ከሃይማኖት፣ ከቀኖናዊ ትውፊትም፣ ከአስተዳደራዊ መዋቅርም በመውጣት ራሳቸውን ከቤተ ክርስቲያን መንበር የለዩ በመሆኑ” ድርጊቱን ማውገዙን አስፍሯል።
ቅዱስ ሲኖዶሱ ከቤተ ክርስቲያኗ አውግዤ ከክህነት ሥልጣናቸውን ሽሬያለሁ ያላቸው በኤጲስ ቆጶስነት በቅርቡ የተሾሙት አባ ዘስላሴ ማርቆስ፣ አባ ኃይለሚካኤል አረጋይ፣ አባ እስጢፋኖስ ገብረ ጊዮርጊስ፣ አባ መሃሪ ሃብቶ፣ አባ ኤልያስ ታደሰ ገብረ ኪዳን፣ አባ ጽጌገነት ኪዳነ ወልድ፣ አባ ዘርዓዳዊት ብርሃነ፣ አባ ዮሃንስ ከበደ፣ አባ የማነ ብርሃን ወልደ ሳሙኤልን ነው።
በተጨማሪም ሲመቱ እንዲፈጸም ከጽንሰ ሃሳብ ጀምሮሲኖዶሱ መሪና ቀስቃሽ ናቸው ያላቸው በትግራይ ቤተ ክህነት በኤጲስ ቆጶስነት ዕጩ የሆኑትን እና በቅርቡ ከአዲስ አበባ በአስገዳጅ መልኩ ወደ አውስትራሊያ እንዲመለሱ የተደረጉት አባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤልን ማውገዙን እና ከቤተ ክርስቲያኗ መለየቱን አስታውቋል።
በተጨማሪም የትግራይ ቤተ ክህነት ዋና ፀሃፊ መምህር ተስፋዬ ሃደራም በዋና አስፈጻሚነት በመምራት እና መግለጫ በመስጠትም እየተሳተፉ በመሆናቸውም ከተወገዙት መካከል መሆናቸውን አስታውቋል።
ሆኖም ቤተ ክርስቲያኗ አባቶቹ “በሰሩት የቀኖና ጥሰት ተጸጽተው ይቅርታ ቢጠይቁ የቤተ ክርስቲያን በር ክፍት መሆኑን እና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንቀበላቸዋለን” ሲልም አስፍሯል።
በተጨማሪም ደም አፋሳሹን ጦርነት ተከትሎ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በመለየት በትግራይ አባቶች የተቋቋመው መንበረ ሰላማ የሚለውም “ሕገወጥ ስያሜ በቤተ ክርስቲያኗ ትውፊት የማይታወቅ፣ ሃይማኖታዊ መሠረት የሌላው፣ አስተዳደራዊ መዋቅርን የሚያዛባ” በመሆኑ ቤተ ክርስቲያኗ አትቀበለውም ብሏል።
መንበረ ሰላማ የሚለውም ስያሜ ቤተ ክርስቲያኗን የማይወክል በመሆኑም በመላው ዓለም ለሚመለከተው ሁሉ በደብዳቤ እንዲገለጽም የሚል ውሳኔ አስተላልፏል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስምን ከፊትም ሆነ ከኋላ በመጨመር እና በመቀነስ በከፊልም ሆነ በሙሉ መጠቀም፣ ዓርማ፣ አድራሻዋን፣ የአምልኮ እና የሥርዓት መፈጸሚያ የሆኑ ንዋየ ቅዱሳትን እና አልባሳት እንዲሁም መጻህፍት መገልገል እንደማይቻል የጠቀሰው ይህ መግለጫ፣ ይህንንም የሚከታተል ሃገር እና አለም አቀፍ የህግ ባለሙያዎች ኮሚቴ እንዲቋቋም አቅጣጫ አስቀምጧል።
በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያኗ ያወገዘቻቸው የትግራይ ጳጳሳት እና ኤጲስ ቆጶሳት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የማይወክሉ እና ምንም ዓይነት የሥራ ግንኙነት የሌላቸው መሆናቸውን ለሌሎች ዓለም አቀፍ አብያተ ክርስቲያናት በጽሁፍ እንዲገለጽ ተብሏል።
ለሁለት ዓመታት በትግራይ ውስጥ በተካሄደው ጦርነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሲኖዶስን ለፌደራሉ መንግሥት በመወገን በገንዘብ እና በቅስቀሳ በጦርነቱ ተሳትፋለች ብለው የትግራይ አባቶች ይወቅሷታል። በተጨማሪም በትግራይ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተቋማት ውድመት እና ምዕመናን ላይ ግድያ ሲፈጸም ሲኖዶሱ ዝምታን መርጧል በማለትም ይወቅሱታል።
ቅዱስ ሲኖዶሱ በትግራይ ውስጥ በተካሄደው ጦርነት ወቅት የቤተክርስቲያኗን አባቶች እና ምዕመናንን ደኅንነት በተመለከተ አስፈላጊውን ሁሉ ባለማድረጉ ይቅርታ መጠየቁን ቢገልጽም፣ ከትግራይ አባቶች ዘንድ በቂ አይደለም የሚል ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል።
በተጨማሪም በፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ የሚመራ የልዑካን ቡድን ከትግራይ አባቶች ጋር ለመነጋገር ወደ መቀለ ቢያቀናም የትግራይ አባቶች በውይይቱ ላይ ባለመገኘታቸው ንግግሩ አለመካሄዱ የሚታወስ ሲሆን፣ በኋላም የትግራይ ቤተ ክህነት “ውይይቱን በተመለከተ የደረሰን ደብዳቤ የለም” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።