የገዛ መሪዎቻቸውን ፍርድ ቤት ያቆሙ አገራት የትኞቹ ናቸው?
ዶናልድ ትራምፕ የሰሞኑ ዜና ነበሩ። በአሜሪካ ታሪክ በወንጀል የተከሰሱ የመጀመርያው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሆነዋል።
በሌሎች አገራት ይህ ሆኖ ያውቃል?
ዋና ዋናዎቹን ቀጥለን እንመለከታለን።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ጣሊያን፡ ሲልቪዮ በርልስኮኒ
ጣሊያንን በተደጋጋሚ የመሩት ሽማግሌው በርልስኮኒ በዓለም እንደርሳቸው በተደጋጋሚ የተከሰሰ መሪ የለም ይባልላቸዋል።
በዚህ ሰዓት ጤናቸው ተጓድሎ ጽኑ የሕሙማን ክፍል ውስጥ ናቸው።
በርልስኮኒ መዝናናትን አብዝተው የሚወዱ ናቸው። የቀድሞው የሊቢያ መሪ ሟቹ ጋዳፊ ወዳጅም ነበሩ።
በ2013 ዓ/ም በርልስኮኒ ለአቅመ ሔዋን ካልደረሰች ልጃገረድ ጋር በወሲብ ታምተው ተከሰዋል። ይህ በታሪክ ‘ቡንጋ ቡንጋ” በሚል ይታወቃል። በርልስኮኒ በሚያሰናዷቸው የግል ድግሶች ልጃገረዶችን በመጋበዝ የልጅ ልጆቻቸው ከሚሆኑ ሴቶች ጋር ይባልጋሉ እየተባሉ ይታሙ ነበር።
ከዚህ ክስ ነጻ የወጡት በፈረንጆቹ 2015 ነው።
በ2012 ደግሞ ግብር አጭበርብረዋል ተብለው ተከሰው ነበር። እስሩ ቀርቶላቸው የማኅበረሰብ በጎ ሥራ እንዲሰሩ ተፈርዶባቸዋል።
ከዚያ ደግሞ የተቀናቃኛቸውን ስልክ አስጠልፈው ምሥጢሩ በጋዜጣ ለአደባባይ እንዲጋለጥ አድርገዋል በሚል አንድ ዓመት ተፈርዶባቸዋል።
በርልስኮኒ የእግር ኳስ ቡድንን ጨምሮ የበርካታ ጋዜጦች ባለቤት ነበሩ።
የሚደንቀው ይህን የአንድ ዓመት ፍርድም አልፈጸሙትም። ዕድሜያቸው ገፍቷል በሚል ታልፈዋል።
አሁን በሚላን ሆስፒታል ሕክምና ላይ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ብራዚል፡ ሉላ ዳ ሲልቫ
ሉላ ዳ ሲልቫ ፕሬዝዳንት ነበሩ። ተፈረደባቸውና ዘብጥያ ወረዱ። አሁን ተመልሰው ደግሞ ፕሬዝዳንት ሆነዋል።
ከአንድ የሕንጻ ተቋራጭ ገንዘብ ተቀብለዋል ተብለው ነው ሉላ ለእስር የተዳረጉት። ተቋራጩ ገንዘቡን ለሉላ ሲልቫ የሰጣቸው በብራዚል ነዳጅ ድርጅት (ፔትሮብራስ) ሥራ እንዲያገኝ በሚል ነበር።
የብረት ባለሙያ የነበሩት ሉላ ሲልቫ 580 ቀናትን በእስር አሰልፈዋል። በ2018 ደግሞ ምርጫ እንዳይሳተፉ ተደርጓል።
“በሕይወት ሳለሁ ሊቀብሩኝ ነበር የሞከሩት፤ እንደምንም ተነሳሁ” ብለዋል ሉላ በድጋሚ ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ።
ሉላ ዳ ሲልቫ የቀኝ አክራሪውና የላቲኑ ትራምፕ ይባሉ የነበሩትን ዣየር ቦልሶናሮን በማሸነፍ ነው ለሥልጣን የበቁት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ደቡብ ኮሪያ፡ ፓርክ ዮን ሔ
ፓርክ የደቡብ ኮሪያ የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ናቸው። የመጀመርያዋ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ሥልጣን ይዘው በሙስና ቅሌት ከሥልጣን የተባረሩ መሪም ናቸው።
የተከሰሱት እንደ አውሮፓዊያኑ በ2017 ነበር።
ከባለእንጀራቸው ጋር ሥልጣናቸውን ተጠቅመው የሕዝብ ሃብትን ለምዝበራ አጋልጠዋል በሚል ነው የተከሰሱት።
ባልንጀራቸው ቾይ ይባላሉ። ቾይ የፕሬዝደንት ፓርክን መልካም ግንኙነት ተጠቅመው ከባለሃብቶች ጋር ሚሊዮን ዶላሮችን በእርዳታ መልክ ማግኘት ችለዋል።
ፓርክ የተወሰኑ ዓመታትን እስር ቤት ካሳለፉ በኋላ ይቅርታ ተደርጎላቸው በፈረንጆቹ 2021 ዓ/ም ከእስር ተለቀዋል።
ፈረንሳይ፡ ኒኮላስ ሳርኮዚ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ሳርኮዚ በሪፐብሊክ ፈረንሳይ ዘብጥያ እንዲወርዱ የተፈረደባቸው የመጀመርያው ፕሬዝዳንት ሆነዋል።
ይህም በ2021 ዓ/ም ነበር። የተከሰሱት ዳኛን በጉቦ ለመደለል ሞክረዋል በሚል ነው።
ፍርዱ ግን እስከዛሬም አልጸናም። ሁለት ዓመት ተፈርዶባቸው የነበሩ ቢሆንም ይግባኝ ብለው አሁንም ድረስ ጉዳዩ በፍርድ ላይ ነው።
በእርግጥ ከእርሳቸው በፊት የነበሩት ዣክ ሺራክም በ2011 በተመሳሳይ ጥፋተኛ ተብለው የሁለት ዓመት ፍርድ በይርጋ ታልፎላቸዋል።
ደቡብ አፍሪካ፡ ጃኮብ ዙማ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ዙማ 15 ወራት እስር ነው የተፈረደባቸው። ለዚህ ያበቃቸው ሙስና አጣሪ የፍርድ ሸንጎ እንዲቀርቡ ተብለው ባለመቅረባቸው ነው።
ዙማ ለፖሊስ እጅ ከመስጠታቸው በፊት ረብሻ ተነስቶ ከ 300 ሰዎች በላይ ሞተዋል።
ዙማ ከዚህ ሌላ የማጭበርበርና ሙስና ክስ አለባቸው።
ማሌዥያ፡ ናጂብ ራዛክ
የቀድሞው የማሌዥያ ጠቅላይ ሚኒስትር በርካታ ሚሊዮን ዶላሮችን ዘርፈዋል በሚል ነው 12 ዓመት የተፈረደባቸው።
ናጂብ እኔ አማካሪዬ አሳስቶኝ ነው እንጂ ንጹህ ነኝ ይላሉ። ናጂብ ይግባኛቸው ውድቅ ተደርጎ ከነሐሴ ጀምሮ በእስር ላይ ናቸው።
ከዚህ የሙስና ክስ በተጨማሪ ሌሎች ክሶችም ይጠብቋቸዋል።
እስራኤል፡ ኢሁድ ኦልመርት
የእስራኤሉ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢሁድ ኦልመርት 2 ዓመት ከሦስት ወር ተፈርዶባቸው ይህንኑ ፍርድ የጨረሱት በ2017 ነበር።
ፍርዱ የጸናባቸው በማጭበርበር ክስ ቀርቦባቸው ነው።
ኦልመርት ከዚያ በኋላ ከፖለቲካ ጡረታ ቢወጡም ቤንጃሚን ናታንያሁን በክፉ አንስተው ስም አጠልሽተዋል በሚል ሌላ ክስ ቀርቦባቸዋል።
ናታንያሁ ራሳቸው ጉቦ በመስጠት፣ እመነት በማጉደልና በሙስና ያልተቋጨ ክስ አለባቸው።
ናታንያሁ ለረዥም ዘመን እስራኤልን በመምራት ተወዳዳሪ የላቸውም።
ታይላንድ፡ ዪንግላክ ሺናዋትራ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ሺናዋትራ የቀድሞ የታይላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው።
የተከሰሱ የነበረው ሙስናን ባለማስቆም ቸልተኝነት ነበር።
በ2014 መንግሥታቸው ተገለበጠ። እርሳቸው ክሱ የፖለቲካ ቂም በቀል ነው ይላሉ።
በ2017 አገራቸውን ለቀው ቢሰደዱም በሌሉበት አምስት ዓመት ተፈርዶባቸዋል።
ቦሊቪያ፡ ጄኒን አንየዝ
የቀድሞ የቦሊቪያ ፕሬዝዳንት ጄኒን 10 ዓመት የተፈረደባቸው ተቀዳሚያቸውን ኢቮ ሞራሌስን ለመገልበጥ ሞክረዋል በሚል ነው።
ሞራሌስ ሥልጣን ለቀው ከአገር ተሰደው ነው ያሉት።
የሞራሌስን አገር መልቀቅ ተከትሎ ጄኒን ጊዝያዊ ፕሬዝዳንት ሆነው ተⶄሙ።
ይሁንና የሞራሌስ ፓርቲ በቀጣዩ ዓመት ጠቅላላ ምርጫ አሸነፈና ሞራሌ ከተሰደዱበት አርጀንቲና ተመለሱ። ባልደረባቸው ሉዊስ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ።
ጄኒን በተደጋጋሚ የፖለቲካ ብቀላ ተፈጽሞብኝ ነው እስር ቤት ያለሁት ይላሉ።












