የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የትራምፕን ቬንዙዌላውያንን ከአገር የማባረር ውሳኔ አገደ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር የቬንዙዌላ የወሮበሎች ቡድን አባላት ናቸው ብሎ የከሰሳቸውን ሰዎች ከአገር ማስወጣት እንዲያቆም አዘዘ።
በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በጦርነት ጊዜ የወጣ ሕግን መሠረት አድርጎ መንግሥት በሰሜን ቴክሳስ አስሯቸው የሚገኙትን ቬንዙዌላውያንን ከአገር ለማባረር ያወጣውን ዕቅድ በመቃወም የዜጎች ነፃነት ቡድን ነው ክሱን የመሠረተው።
ቅዳሜ እለት ጠቅላይ ፍርድ ቤት መንግሥት "ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ትዕዛዝ እስኪሰጥ ድረስ ማንኛውንም የወንጀል ቡድን አባል ለው ተብሎ የተጠረጠረ እስረኛ ከዩናይትድ ስቴትስ እንዳይወጣ" አዟል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት የ"ጠላት" አገር ተወላጆች ወይም ዜጎች የተለመዱ ሂደቶችን ሳይከተሉ እንዲታሰሩ እና እንዲባረሩ ለማዘዝ የሚያስችል ሥልጣን የሚሰጠውን የ1798 የውጭ አገር ጠላቶች ሕግን በመጥቀስ ነበር ቬንዙዌላውያኑ እንዲያዙ እና ከአገር እንዲባረሩ ያዘዙት።
ትራምፕ የቬንዙዌላውን ትሬን ደ አራጓ (ቲዲኤ) የተባለው የወሮበላ ቡድን በአሜሪካ ግዛት ላይ "ወረራ ፈጽሟል፣ ሞክሯል እና አስፈራርቷል" ሲል ከሰዋል።
ከ261 ቬንዙዌላውያን ከሚያዚያ መጀመሪያ አንስቶ አደገኛ ወደሚባለው የኤል ሳልቫዶር ግዙፍ እስር ቤት ከተባረሩ 137ቱ በውጭ አገር ጠላቶች ሕግ መሠረት ከአገር የተባረሩ መሆናቸውን አንድ ከፍተኛ የአስተዳደር ባለሥልጣን በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ለሲቢኤስ ተናግረዋል።
ይህንን የፕሬዝዳንቱን ከአገር የማባረር ውሳኔ በመጋቢት አጋማሽ ላይ የአሜሪካ የሥር ፍርድ ቤት ጊዜያዊ እግድ ጥሎበት ነበር።
ጠቅላይ ፍርድ ቤት መጀመሪያ ላይ ከሳምንት በፊት ትራምፕ በወሮበላ ቡድን አባልነት የተጠረጠሩትን ከአገር ለማባረር የውጭ ጠላቶች ሕግን ሊጠቀሙ ይችላሉ ሲል የወሰነ ቢሆንም፣ ነገር ግን የሚባረሩት ሰዎች ውሳኔውን በፍርድ ቤት ለመቃወም ዕድል ሊሰጣቸው ይገባል ብሏል።
የፍትህ አካላት በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በውሳኔያቸው ላይ "ማስጠንቀቂያው ምክንያታዊ በሆነ የጊዜ ገደብ ውስጥ መሰጠት አለበት እንዲሁም በትክክለኛው ቦታ ላይ እራሳቸውን የመከላከል እንዲያገኙ በሚያስችል መልኩ መቅረብ አለበት" ብለዋል ።
አሁን የወጣውን ዕግድን ያስወሰነው የአሜሪካ የሲቪል ነፃነቶች ልብረት ክስ በሰሜን ቴክሳስ ለእስር የተዳረጉት ቬንዙዌላውያን የስፓኒሽ ቋንቋ ብቻ ቢናገሩም ማስጠንቀቂያው በእንግሊዘኛ ተሰጥቷቸዋል፣ በቅርቡ እንደሚባረሩ እና በፌዴራል ፍርድ ቤት ውሳኔውን የመቃወም መብት እንዳላቸው አልተነገራቸውም ብሏል።
"ያለ ፍርድ ቤት ጣልቃ ገብነት፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የወንጀለኛ ቡድን አባላት ተብውለ የመባረር ውሳኔ የተላላፈባቸው ሰዎች በኤል ሳልቫዶር ውስጥ የዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ሊደረጉ ይችላሉ፣ የተከሰሱበትን የወሮበላ ቡድን አባልነት ስያሜን ወይም ከአገር መባረራቸውን ለመቃወም የሚያስችል ትክክለኛ ዕድል እንዳላገኙ" ክሱ አመልክቷል።












