በብዙ የተፈተነችው እንግሊዝ እና ስፔን ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቀሉ

ጁድ ቤሊንግሃም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ እንግሊዝ እና ስፔን ሩብ ፍጻሜውን መቀላቀላቸውን አረጋገጡ።

ትላንት በቅድሚያ የተገናኙት እንግሊዝ እና ስሎቫኪያ ነበሩ።

እንግሊዝ ከውድድሩ የተሰናበትች መስሎ ነበር። የጨዋታው መደበኛ 90 ደቂቃ አብቅቶ በተጨማሪ ሰዓት ላይ ጁድ ቤሊንግሃም አገሩን መታደግ ችሏል።

ስሎቫኪያ ጨዋታው በተጀመረ በ25ኛው ደቂቃ በኢቫን ሽራንዝ አማካኝነት ቀዳሚ ለመሆን ችላ ነበር።

እንግሊዝ በምድብ ጨዋታዎች ሁሉ በምሽቱ ግጥሚያም ይህ ነው የሚባል ነገር ማሳየት ተስኗታል አምሽታለች።

ጨዋታው አንድ ለምንም ሊጠናቀቅ ጥቂት ሰከንዶች በቀሩበት እና በርካታ የእንግሊዝ ደጋፊዎች ተስፋ በቆረጡበት በተጨማሪው ሰዓት መጠናቀቂያ ላይ ጁድ ቤሊንግሃም ድንቅ ጎል አስቆጥሮ አንግሊዝን አቻ አደረገ።

በዚህ ውጤት የተጠናቀቀው ጨዋታ ወደ ተጨማሪ ሰዓት ያመራ ሲሆን በተጨማሪው ሰዓት መጀመሪያ ደቂቃ ሃሪ ኬን ባስቆስጠረው ጎል እንግሊዝ 2 ለ 1 ለመምራት በቃች።

ጨዋታው በዚህ ውጤት ተጠናቆ እንግሊዝ ሩብ ፍጻሜውን ብትቀላቀልም ብዙ ማሻሻል ያሉባት ነገር እንዳለ የታየበት ጨዋታ ሆኖ አልፏል።

ውጤቱን ተከትሎም እንግሊዝ በሩብ ፍጻሜው ከስዊትዘርላንድ ጋር የምትፋለም ይሆናል፡፡

በሁለተኛው ጥሎ ማለፍ ጨዋታ ደግሞ ስፔን ከጆርጂያ ነበር የተገናኘችው። ስፔን በጆርጂያ በትፈተንም በሰፊ የግብ ልዩነት በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍጻሜው መቀላቀሏን አረጋግጣለች።

ስፔን ከመጀመሪያው ደቂቃ ጀምሮ ጫና ብታሰድርም ለመጀመሪያ ጊዜ ትልቅ ውድድር ላይ የተሳተፈችው ጆርጂያ ጎል ማስቆጠር ችላለች።

ጎሉ በራሱ መረብ ላይ ያሳረፈው የስፔኑ ተከላካይ ሮቢን ል ኖርማንድ ነው።

በዚህ ጎል ያልደበዘዙት ስፔኖች ማጥቃታቸውን በማጠናከር በሮድሪ ጎል አቻ ለመሆን ችለዋል።

በውድድሩ ድንቅ ብቃታቸውን ካሳዩት መካከል አንዷ የሆነችው ስፔን በፋቢያን ሩዊዝ፣ ኒኮ ዊሊያምስ እና ዳኒ ኦልሞ አማካኝት ጎሎችን አስቆጥራ ጨዋታውን 4 ለ 1 አሸንፋለች።

ከፍጻሜ በፊት የፍጻሜ ጨዋታ በተባለለት ጨዋታ በሩብ ፍጻሜው ስፔን እና ጀርመን የሚገናኙ ይሆናል።

የአውሮፓ ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ዛሬም የሚቀጥሉ ሲሆን ፈረንሳይ እና ቤልጂዬም የሚያደርጉት ጨዋታ ደግሞ ተጠባቂ ነው።

በሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ ፖርቹጋል እና ስሎቬኒያ የሚጫወቱ ይሆናል።