ፕሬዚዳንት ፑቲን አገራቸው ከአፍሪካ ጋር ላላት ግንኙነት ቅድሚያ እንደምትሰጥ አስታወቁ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በዩክሬን ወረራ ምክንያት ከምዕራቡ ዓለም ማዕቀብ የተጣለባቸው የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን አገራቸው ከአፍሪካ ጋር ላላት ግንኙነት ቅድሚያ ትሰጣለች ብለዋል።
“አገራችን ከአፍሪካ አገራት ጋር ለመተባበር ቅድሚያ እንደምትሰጥ እና በዚህም እንደምትቀጥል አጽንኦት መስጠት እፈልጋለሁ” ሲሉም ፕሬዚዳንት ፑቲን ትናንት ሰኞ ሞስኮ በተካሄደው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ላይ ተናግረዋል።
ከዩክሬን በሚቀርበው እህል ላይ የተደረሰው ስምምነት ካልታደሰ ሩሲያ ለተቸገሩ የአፍሪካ አገራት በነጻ እህል እንደምታቀርብም ነው ፑቲን ቃል የገቡት
“በባለፉት ዓመታት ሲላክ የነበረውን የእህል መጠን ለአፍሪካ አገራት በተለይም ከሩሲያ ለሚፈልጉ በነጻ ለማቅረብ ዝግጁ ነን” ሲሉ መናገራቸውን የሩሲያ የዜና ወኪል ታስ ዘግቧል።
ፕሬዚዳንት ፑቲን ሩሲያ የደረሰችባቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለአፍሪካ አገራት እንደምታካፍል እና የኤሌክትሪክ ሀይል እንዲያመርቱ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም ተናግረዋል።
ሩሲያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአፍሪካ ተጽእኖዋን እያሰፋች የምትገኝ ሲሆን “ አህጉሪቱ እያቆጠቆጠ ባለው የብዝኃ የዓለም ስርዓት ላይ ስልጣኗን እና ሚናዋን ማሳደግ እንደምትቀጥል አምናለሁ” ብለዋል።
በጉባኤው ላይ ከ40 በላይ የአፍሪካ አገራት ልዑካን እየተሳተፉ መሆኑንም የክሬምሊን የፕሬስ አገልግሎት ዘግቧል።
በመጪው ሰኔ ወር ላይ ሁለተኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ የሚካሄድ ሲሆን ፕሬዚዳንቱ የአፍሪካ መሪዎችን ይቀበላሉ።












