ፑቲን የሚሳኤል ዛቻ እንደሰነዘሩባቸው የቀድሞው የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ተናገሩ

የቀድሞ የዩኬ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቀድሞ የዩኬ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን
ታትሟል

የዩኬው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የሩሲያው ፑቲን ከዩክሬኑ ጦርነት በፊት የሚሳኤል ጥቃት ዛቻ እንደሰነዘሩባቸው ተናገሩ።

ቦሪስ ይህን ያሉት በቅርብ በቢቢሲ ለሕዝብ በሚተላለፈው ፑቲንና ምዕራቡ ዓለም የሚል ዘጋቢ ፊልም ላይ ነው።

ቦሪስ ጆንሰን እንዲህ ዐይነት ያልተጠበቀ ዛቻ በፑቲን ደረሰብኝ ያሉት ሩሲያ ዩክሬንን ለመውረር 15 ቀናት ሲቀራት እንደሆነ አስረድተዋል።

ፑቲን ወረራ እንደሚያደርጉ ስለታወቀ ይህን ለማስቆም ከፍተኛ ማግባባት በተያዘበት ወቅት ቦሪስ ጆንሰን ዘለግ ላለ ሰዓት ከፑቲን ጋር በስልክ ተነጋግረዋል።

በዚህ የስልክ ንግግር ወቅት ፑቲን በእንግሊዝኛ “ልጎዳህ አልፈልግም፤ ነገር ግን ሚሳኤል ልንተኩስብህ እንችላለን፤ ይህ ደግሞ አንድ ደቂቃ ነው የሚወስድብን” ብለው እንዳስፈራሩ ቦሪሰ አስታውሰዋል።

ፑቲን ይህን ያሏቸው ቦሪስ ጆንሰን ይህ ጦርነት ከተጀመረ “በጣም ረዥም ጦርነት ነው የሚሆነው፤ በቶሎ አያባራም፤ ጥፋቱም ከፍተኛ ነው” ብለው ካስረዱ በኋላ እንደሆነ ለቢቢሲ መስክረዋል።

ከዚህም በላይ ራሺያ ዩክሬንን ከወረረች ምዕራቡ ዓለም ከፍተኛ የሚባል ማዕቀብ ሊጥልባት እንደሚችል፤ የኔቶ ወታደሮችም ወደ ሩሲያ ድንበር ሊጠጉ እንደሚችሉ አብራርተውላቸው ነበር።

ይህን አብራርተው ካበቁ በኋላ ዩክሬን ለሚቀጥሉት መጪ ዓመታት ኔቶን እንደማትቀላቀል ማረጋገጫ ለፑቲን እንሰጧቸው ጠቅሰዋል።

ከዚህ ማብራሪያ በኋላ ነበር ፑቲን “ልጎዳህ አልፈልግም ነገር ግን በሚሳኤል ይህን ለማድረግ አንድ ደቂቃ ቢወስድብን ነው” ሲሉ ዛቻ የሚመስል ነገር የተናገሩት።

ቦሪስ እንዳሉት የፑቲን ዛቻ ከልባቸው ይሁን ለማስፈራራት ማወቅ አልቻሉም።

ይሁንና ከዚህ ቀደም ሩሲያ በዩኬ ላይ በ2018 ሳሊስበሪ ላይ ከፈጸመችው ጥቃት አንጻር ሲታይ ዛቻውን በዋዛ እንደማያዩት አስረድተዋል።

ከዚህ የስልክ ንግግር ዘጠኝ ቀናት በኋላ የዩኬ መከላከያ ሚኒስትር ቤን ዋላስ ወደ ሞስኮ ሄደው አቻቸውን ሰርጌ ሾይጉን ማግኘታቸውን ተናገረዋል።

መከላከያ ሚኒስትር ዋለስ ለዚህ ቢቢሲ ዘጋቢ ፊልም ሲናገሩ ከውይይት በኋላ ሩሲያ ዩክሬንን እንደማትወር ማረጋገጫ ሰጥታ ነበር።

“ይሁንና እንደዋሸችን እኛም እናውቅ ነበር፤ እነርሱም ያውቃሉ። እኛም እንደሚያውቁ እናውቅ ነበር፤ እነርሱም እንዳወቅን ያውቁ ነበር” ብለዋል።

የወቅቱን ሁኔታ በሌላ ቋንቋ ሲያስረዱ፣ “እየዋሸሁህ ነው፤ እየዋሸሁ እንደሆነ አንተም ታውቃለህ፤እየዋሸሁ እንደሆን አንተ እንደምታውቅ እኔም አውቃለሁ፤ ቢሆንም ግን መዋሸቴን እቀጥላለሁ” እንደማለት ነው።

ዋለስ እንዳሉት ከዚህ ንግግር ከጥቂት ሳምንት በኋላ ወረራው እውን ሆነ።

ቦሪስ ጆንሰን ለዚህ ዘጋቢ ፊልም እንዳሉት ወረራው በተፈጸመ ዕለት እኩለ ሌሊት ላይ ዜለነስኪ እንደደወሉላቸው አስታውሰዋል።

“በየአቅጣጫው ጥቃት ከፍተውብናል” ሲል ዜለንስኪ ነገረኝ ካሉ በኋላ ለፕሬዝዳንት ዜለነስኪ ከአገር እንዲወጡ ከለላ እንደሚሰጧቸው ሲነግሯቸው ግን ፍቃደኛ እንዳልሆኑ አስታውሰዋል።

ዜለነስኪ አገራቸው ቆይተው ጦርነቱን እየመሩ ይገኛሉ።

“ፑቲንና ምዕራባዊያኑ” የሚለው የቢቢሲ ዘጋቢ ፊልም ከነገ ጀምሮ ለሕዝብ እንደሚሰራጭ ይጠበቃል።