እስራኤል በራፋህ ላይ ለምትፈፅመው የምድር ጥቃት ቀነ ገደብ አስቀመጠች

የፎቶው ባለመብት, REUTERS
ሐማስ በጋዛ የታገቱ ሁሉንም እስራኤላውያን ካለቀቀ በመጋቢት 01፣ 2016 ዓ.ም በራፋህ ላይ የምድር ጥቃት እንደሚከፈት የእስራኤል የጦር ካቢኔ አባል ቤኒ ጋንትዝ አስጠነቀቁ።
እስራኤል በተፈናቃዮች በተጨናነቀችው ደቡባዊቷ ከተማ ራፋህ ወታደሮቿ ሊገቡ እንደሚችሉ ስትገልጽ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ሆኖም እስራኤል 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን በተጠለሉባት ራፋህ ላይ ለመፈፀም ያቀደችው ጥቃት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተቃውሞ ገጥሞታል።
ቀደም ብሎ የተባበሩት መንግሥታት የሕብረተሰብ ጤና ኤጀንሲ እንደገለጸው እስራኤል በፈፀመችው ጥቃት በጋዛ የሚገኘው ዋና ሆስፒታል ሥራ አቁሟል።
የዓለም ጤና ድርጅትም በሆስፒታሉ ያለውን ሁኔታ ለመገምገም በሰሜን ራፋህ፣ ኻን ዮኒስ ከተማ በሚገኘው ናስር ሆስፒታል ለመግባት እንዳልተፈቀደለት ገልጿል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል በሐማስ ታግተው የተወሰዱ እስራኤላውያን በሆስፒታሉ ውስጥ እንደሚገኙ የደኅንነት መረጃዎቼ ጠቁመዋል በማለት ወደ ሆስፒታሉ በመግባት ጥቃት የከፈተው ሐሙስ ዕለት ነበር።
መከላከያ ኃይሉ ሐማስ “ሆስፒታሉን ለሽብር ተግባር ተጠቅሞባታል” ሲል በመክሰስ በናስር ሆስፒታል ላይ የከፈተውን ዘመቻ “ ትክክለኛ እና ውስን “ ሲል ገልጾታል።
የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር ጋንትዝ እሑድ ዕለት ሲናገሩ “ በረመዳን ጾም መጀመሪያ ታጋቾቻችን ወደ ቤታቸው ካልገቡ ራፋህን ጨምሮ በሁሉም ቦታዎች ውጊያው እንደሚቀጥል ዓለምም ሆነ የሐማስ መሪዎች ሊያውቁ ይገባል” ብለዋል።
በዚህ ዓመት እስላማዊው ቅዱስ ወር ረመዳን የሚጀምረው መጋቢት 01፣2016 ዓ.ም ነው።
የቀድሞው ሚኒስትሩ ጨምረውም እስራኤል በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ከአሜሪካ እና ከግብፅ አጋሮቿ ጋር በመነጋገር ከአካባቢው የሚወጡበትን መንገድ ታመቻቻለች ብለዋል።
ጋንትዝ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ከግብፅ ጋር እንደሚሰሩ መጠቆማቸው፣ እስራኤል የተወሰኑ ፍልስጤማውያን ከጋዛ ሰርጥ በመውጣት ከፍተኛ ግንባታ እየተካሄደበት ነው በተባለው የግብጽ ድንበር ላይ እንዲጠለሉ ትፈልጋለች የሚለውን መረጃ እንደሚያጠናክር የቢቢሲ የዲፕሎማቲክ ዘጋቢ ፖል አዳምስ ተናግሯል።
ነገር ግን የእስራኤል ባለሥልጣናት ሰላማዊ ሰዎችን ከአካባቢው ስለሚያስወጡበት እቅድ በዝርዝር አልገለጹም ብሏል።
የእስራኤል የጦር ካቢኔ ከፍተኛ የጸጥታ ባለሥልጣናትን የያዘ ሲሆን በሐማስ የተመራው ታጣቂ ቡድን ጥቅምት ወር ላይ በአገሪቷ ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመክፈት ቢያንስ 1 ሺህ 200 ሰዎችን ከገደለ እና 253 ሰዎችን አግቶ ከወሰደ ከቀናት በኋላ የተቋቋመ ነው።
እስራኤል ሐማስ 130 የሚሆኑ እስራኤላውያንን በጋዛ አግቶ ይዟል ብላ ታምናለች።
ከራፋህ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ጥቂት ሰዎች አካባቢውን ለቀው ወደ ባህር ዳርቻው እየወጡ ሲሆን አብዛኞቹ ደግሞ የሚያደርጉት ቸግሯቸው እዚያው እየጠበቁ ይገኛሉ።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና ቢያሳድርም የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ የሐማስ ታጣቂዎችን ለማጥፋት በራፋህ ላይ የምድር ጥቃት እንደሚከፍቱ ዝተዋል።
ግብፅ እና ሌሎች የአረብ አገራት እስራኤል በራፋህ ላይ የምትፈፅመው ጥቃት በርካታ ፍልስጤማውያን ወደ ግብፅ እንዲሰደዱ ይገፋፋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ሳዑዲ አረቢያም ራፋህ ላይ ጥቃት የሚፈፀም ከሆነ ከፍተኛ ቀውስ እንደሚያስከትል ጥርጥር እንደሌላት ገልጻለች።
በመሆኑም እስራኤል በራፋህ ላይ ለመፈፀም ካቀደችው ጥቃት እንድትታቀብ በርካታ አገራት ጥሪ እያቀረቡ ነው።
እስራኤል ከጥቅምት ወር ጀምሮ የጋዛ ሰርጥን ወደ ፍርስራሽነት የቀየረውን የማያባራ ጥቃት ስትፈፅም ቆይታለች።
ጦርነቱ ከጀመረ አንስቶም በአብዛኛው ሕጻናት እና ሴቶች የሆኑ ከ28 ሺህ 400 በላይ ፍልስጤማውያን ሲገደሉ ከ68 ሺህ በላይ መቁሰላቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ እንዳለው ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ ቢያንስ 127 ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ 205 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በጋዛ የሚካሄደው ውጊያ ቢቀጥልም በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተኩስ አቁም እንዲደረስ የሚደረገው ጥረት ሰሞኑን በካይሮ እየተካሄደ ነው።
ኔታንያሁም በአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን የቀረበላቸውን ጥያቄ ተከትሎ ተደራዳሪዎችን መላካቸውን ገልጸው፣ የሐማስ ፍላጎት የማይጨበጥ ነው በማለት ተደራዳሪዎቻቸው የደረሱበትን ይዘው እስካሁን አለመመለሳቸውን ተናግረዋል።
ሐማስ በበኩሉ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ላለመደረሱ እስራኤልን ተጠያቂ አድርጓል።












