ጋዛ ከግብፅ በምትዋሰንበት ድንበር ላይ ሰፊ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን የሳተላይት ምስሎች አመለከቱ

የፎቶው ባለመብት, MAXAR TECHNOLOGIES
ጋዛ ከግብፅ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር ላይ ትልቅ የግንባታ ሥራ እየተካሄደ መሆኑን የሳተላይት ምስሎች አመለከቱ።
ይህ ግንባታ እየተካሄደ ያለው ለፍልስጤማውያን መጠለያ ለማዘጋጀት እንደሆነ ሪፖርቶች ጠቁመዋል።
ስማቸው ያልተገለጸ የግብፅ ምንጮች እንደተናገሩት እስራኤል በጋዛ ደቡባዊ ክፍል በምትገኘው ራፋህ ከተማ ላይ ለመፈፀም ያቀደችውን የምድር ጥቃት ብትቀጥል በሚል ስጋት ከግብፅ ሰሜናዊ ሲናይ ግዛት የተነጠለ እና የተገለለ ቀጠና ለማቋቋም ነው ግንባታው እየተካሄደ ያለው።
በአንድ የሰብዓዊ መብት ቡድን የወጣ ሪፖርት እንዳመለከተው ከሆነ በአካባቢው ሰባት ሜትር ከፍታ ያላቸው ግንቦች እየተገነቡ ነው።
ግብፅ ግን እያደረገችው ያለ ቅድመ ዝግጅት እንደሌለ ገልጻለች።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮቭ ጋላንትም አገራቸው ሰላማዊ ፍልስጤማውያንን ወደ ግብጽ የማስወጣት ፍላጎት እንደሌላት ገልጸዋል።
ግብፅም የጋዛ ጦርነት ከጀመረ አንስቶ ለስደተኞች ድንበሯን እንደማትከፍት በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች።
አገሪቷ ይህንን አቋም የያዘችው በገፍ የሚሰደዱ ፍልስጤማውያንን በመቀበል ተባባሪ መስሎ ለመታየት ካለመፈለግ ብቻ ሳይሆን ከኢኮኖሚያዊ እና የጸጥታ ስጋት የተነሳ ነው።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እያስጠነቀቀ ቢሆንም 1.4 ሚሊዮን ፍልስጤማውያን ተጠልለው በሚገኙበት ራፋህ ላይ ሰፊ ጥቃት ለመሰንዘር አቅደዋል።
እስራኤል የሐማስ ኃይሎች በከተማዋ እንደሚገኙ በመግለጽ መወገድ ይገባቸዋል ብላለች።
ከዚህም በተጨማሪ እስካሁን የደረሱበት ያልታወቀው 130 የእስራኤል ታጋቾች እዚያ ተይዘው እንደሚገኙም ታምናለች።
በራፋህ ላይ ለመፈፀም የታቀደው ጥቃት ከመጀመሩ በፊትም በዚያ የሚኖሩ ሰላማዊ ሰዎች በከተማዋ ሰሜናዊ አካባቢ ወደሚገኝ ክፍት ቦታ እንዲሄዱ አመላክታለች።
ኔታንያሁ ግልጽ ባልሆነ በንግግራቸው “በሰሜናዊ ራፋህ ወዳፀዳነው አካባቢ” በማለት ተፈናቃዮቹ ስለሚሄዱበት ቦታ ያመላከቱ ሲሆን ፣ ይህ ንግግራቸው ግን ጥቃት የመፈፀም እቅዱ ገና ጅማሬ ላይ ያለ መሆኑን ጠቁሟል።
እስራኤል ቀደም ብሎ በጋዛ ሰሜናዊ ክፍል ጥቃት በጀመረችበት ወቅት ፍልስጤማውያን ሰሜን ጋዛን ለቀው እንዲወጡ እና ወደ ራፋህ እንዲሄዱ ትዕዛዝ ሰጥታ ነበር።
ኔታንያሁ ሐሙስ ዕለት በሰጡት መግለጫም “ ሰላማዊ ሰዎችን ከጦር ቀጠናው እንዲወጡ ካደረግን በኋላ በራፋህ ላይ የሚፈፀመውን ከባድ እርምጃ ጨምሮ ድል እስከምንቀዳጅ ድረስ እንዋጋለን” ብለዋል።
አሁን ላይ በማክሳር ቴክኖሎጂስ የወጡት የሳተላይት ምስሎች ግብፅ በሚፈፀመው ጥቃት ምክንያት ቅድመ ጥንቃቄዎችን ለማድረግ መወሰኗን ይጠቁማሉ።
በአውሮፓውያኑ የካቲት 15 የተነሳው በአንደኛው ምስል ላይ በራፋህ ወደ ጋዛ መሻገሪያ አቅራቢያ የተጸዳ ሰፊ መሬት ያሳያል።
ምስሉ ከአምስት ቀናት ቀደም ብሎ ከነበረው የአካባቢው ምስል ጋር ሲነጻጸር ሥራው ባለፉት ጥቂት ቀናት የተጠናቀቀ ይመስላል።
የግብፅ ሰሜናዊ ሲናይ ግዛት አስተዳዳሪ መሐመድ ሾሻ ለሳዑዲ የዜና አውታር አል አራቢያ አል ሃዳት ቴሌቪዥን ሐሙስ ዕለት እንደተናገሩት በአካባቢው እየተካሄደ ያለው ሥራ ከዚህ በፊት ግብፅ በእስላማዊ ታጣቂ ቡድኑ ላይ በከፈተችው ዘመቻ ወቅት “የፈራረሱ ቤቶችን ለመቁጠር” የተካሄደ ነው።
አስተዳዳሪው ጨምረውም የጋዛ ነዋሪዎችን በግዳጅ በማፈናቀል ወደ ግብፅ እንዲገቡ ማድረግን አትፈቅድም ብለዋል።
እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጅ በሳተላይት ምስሉ ላይ በተጸዳው የድንበር አዋሳኝ ቦታ ላይ ለግንባታ አገልግሎት የሚውሉ ተሽከርካሪዎች የታዩ ሲሆን የተወሰኑት ትልቅ ግድግዳ የሚያቆሙ ይመስላል።
ከሳተላይት ምስሎቹ በተጨማሪም በሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሲናይ ፋውንዴሽን የተነሱ እና የተጋሩ ፎቶዎች እና ቪዲዮዎችም ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን አመልክተዋል።
ተሟጋች ቡድኑ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ባወጣው ሪፖርት ላይ እንዳለው ምስሉ [በቢቢሲ ያልተረጋገጠ] በአካባቢው ሰባት ሜትር ከፍታ ያላቸው ግንቦች እየተገነቡ መሆኑን ያሳያል።
ስለ ጉዳዩ ቅርበት ያላቸውና በሪፖርቱ የተጠቀሱ አንድ ምንጭም “ የጋዛ ስደተኞችን ለመቀበል” ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
ዎል ስትሪት ጆርናል ሪፖርቱን ከግብፅ ባለሥልጣናትና የጸጥታ ጉዳይ ተንታኞች አረጋግጦ፣ ግንባታው በ20.7 ካሬ ኪሎ ሜትር ላይ የሚገነባ ሲሆን ከ100 ሺህ በላይ ሰዎችን መያዝ እንደሚችል ገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣናት እስራኤል በራፋህ ላይ የምድር ጥቃት ለመፈፀም ያወጣችውን እቅድ ተከትሎ የጅምላ ስደት እያንዣበብ እንደሆነ ስጋታቸውን ገልጸዋል። አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ ባለሥልጣንም “ ያለው ሁኔታ ወደዚያው እያመራ ይመስላል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ በጀርመን ሙኒክ የጸጥታ ጉባኤ ላይ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ሲናገሩ ከራፋህ ወደ ግብፅ የሚደረግ ስደት ለፍልስጤማውያን ፣ ለግብጽ እንዲሁም ለወደፊት ሰላም አደጋ እንደሚሆን” አስጠንቅቀዋል።
80 በመቶ የሚሆነው የጋዛ ሰርጥ ሕዝብ በእስራኤል የነጻነት ጦርነት ወቅት ከተሰደዱ አሊያም ከቀያቸው ከተፈናቀሉ ስደተኞች የተወለዱ ናቸው።
ይህንን ጦርነት ተከትሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ቀያቸውን ጥለው የሸሹ ሲሆን፣ ይህንን ክስተት ፍልስጤማውያን “አል ናቅባ” ወይም “መቅሰፍት” ሲሉ ይጠሩታል።
በመሆኑም አሁንም ላይ የአያት ቅድመ አያቶቻቸውን ቤት የሆነችውን ጋዛን ለቀው መውጣት ፍልስጤማውያን ‘ናቅባ’ ብለው የሚጠሩትንና በአውሮፓውያኑ 1948 የተፈጠረውን ጥፋት መድገም እንደሆነ ይቆጥሩታል።
የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ቢኖርም ጋዛን ለቀው መውጣት ለእነርሱ ቀላል አይደለም።
እስራኤል በጋዛ እየፈፀመች ባለችው የማያባራ ጥቃት እስካሁን አብዛኞቹ ሕጻናትና ሴቶች የሆኑ ቢያንስ 28 ሺህ 775 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
እስራኤል በጋዛ ላይ ጥቃት መፈፀም የጀመረችው የሐማስ ታጣቂዎች ጥቅምት ወር ላይ በግዛቷ ዘልቀው በመግባት ባደረሱት ድንገተኛ ጥቃት 1 ሺህ 200 ሰዎችን መግደላቸውን እና 253 ሰዎችን አግተው መውሰዳቸውን ተከትሎ ነበር።












