በዲያስፖራ አካውንት የተቀመጠ ከ20 ሚሊየን ዶላር በላይ ማገዱን የኢትዮጵያ ፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ስም የተቀመጠ ከ22 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ሲታገድ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በበርካታ ሰዎች ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ኢትዮጵያ መንግሥት የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ።
በውጭ አገራት ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተዘረጋውን የባንክ ሥርዓት ባልተገባ መንገድ በመጠቀም ተቀማጭ ተደርጓል የተባለ 22 ሚሊዮን 226 ሺህ ዶላር መታገዱ ተገልጿል።
የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ሰኞ ታኅሣሥ 18/2015 ዓ.ም. በማኅበራዊ ትስስር ገጹ በኩል እንዳስታወቀው፣ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ክትትል ሲያደርግባቸው በቆዩ ድርጊቱ ውስጥ 85 ሰዎች እንደተሳተፉም የጠቆመ ሲሆን ጉዳዩ ወደ ወንጀል ምርመራ መተላለፉንም ገልጿል።
መግለጫው የአገር ውስጥ ባንኮች ለኢትዮጵያውያን እና ለትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚከፍቱትንና የሌሎች ሀገራት ገንዘብ የሚቀመጥበትን የዲያስፖራ አካውንትን ተገቢ ባልሆነ መንገድ በመጠቀም እና “ህግና የአሠራር ስርዓትን በመጣስ የተለያዩ ግለሰቦች በህገ-ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው መገኘታቸውን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ባካሄደው ክትትል ማረጋገጥ ችሏል” ብሏል።
አገልግሎቱ የውጪ ምንዛሬውን ህጋዊ ለማስመሰል ሃሰተኛ ሰነዶች እና “የማጭበርበር ስልቶች” ጥቅም ላይ እንደዋሉም ጠቅሷል።
ከነዚህም መካከል ውጭ ሀገር ሄደው የተመለሱ በማስመሰል ሀሰተኛ ሰነዶችን በማዘጋጀት በማቅረብ የውጪ ምንዛሬን ተቀማጭ ማድረግ አንዱ ስልት መሆኑን ጠቅሷል።
በሌላ በኩል አነስተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ ይዞ በመግባት “ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይዘው እንደገቡ በማስመሰል ቀሪውን በህገ-ወጥ መንገድ ከጥቁር ገበያ ላይ በመሰብሰብና ሀሰተኛ ሰነድ ዲክላራሲዮን በማቅረብ” ህጋዊ ያልሆነ ድርጊት ፈጽመዋል ብሏል።
ሌላኛው ስልት ደግሞ የሌላን ሰው ሰነድ የራስ በማስመሰል እና የዲያስፖራ አካውንት በመጠቀም በህገ ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ ለማስመሰል መሞክር እንዲሁም “ህጉ ከሚፈቅደው ውጪ በተለያዩ ባንኮች የዲያስፖራ አካውንት በመክፈትና በመጠቀም በአጠቃላይ ሌሎች ሀሰተኛ ዲክላራሲዮን በመጠቀም የወንጀል ተግባራት መፈጸማቸውን መረዳት ተችሏል” ብሏል አገልግሎቱ - በመግለጫው።












