የሩሲያን አዲስ ጥቃት በመስጋት ዩክሬን በቤላሩስ በኩል ያለ ድንበሯን ጥበቃ አጠናከረች

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የቤላሩሱ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

ሩሲያ አዲስ ጥቃት ልትሰነዝር ትችላለች በሚል ስጋት ዩክሬን ከቤላሩስ የሚያዋስናት ድንበር ላይ ጥበቃ እያጠናከረች መሆኗን የመንግሥት ባለስልጣን ተናገሩ።

ምክትል የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኢቭሄን ያኒን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ዩክሬን የቤላሩስን ድንበር በጦር ሃይሎች እና መሣሪያዎች አጥራለች።

ይህ ዜና የተገለጸው ቭላድሚር ፑቲን የቤላሩሱን ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ጋር ለመገናኘት ወደ ሚንስክ በተጓዙበት ወቅት ነው።

ቤላሩስ ከሩሲያ እና ከዩክሬን ጋር ድንበር ትጋራለች።

የሩሲያው ፕሬዚዳንት የሃገራቸው ድንበሮች ጥበቃ እንዲጠናከር እና ሩሲያ ውስጥ ማህበራዊ ቁጥጥር እንዲደረግ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

የፀጥታ አካላት የሩስያን ድንበር ለመጣስ የሚደረገውን ማንኛውንም ሙከራ፣ ከውጭ የሚመጡ አደጋዎችን፣ ከዳተኞችና አጥፊዎችን በመለየት በፍጥነት ማክሸፍ አለባቸው ብለዋል።

ልዩ ኃይሎች ሞስኮ ግዛቴ በምትላቸው የዩክሬን ክልሎች የሚኖሩ ሰዎችን ደህንነት ማረጋገጥ አለባቸው ብለዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች (በተለይም በኬርሰን) ሩሲያ በቅርቡ ጉልህ የሆነ ወታደራዊ ሽንፈት አጋጥሟታል።

በቤላሩስ የሰፈረው የሩሲያ ጦር ከቤላሩስ ጋር ወታደራዊ ልምምድ እንደሚያካሂድ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቋል።

ስለጉዳዩ እና ስለጉብኝቱ ምላሽ የሰጡት ዬኒን "በሩሲያ እና በቤላሩስ ላይ የመከላከያ መስመሮቻችንን እየገነባን ነው" ብለዋል።

ቤላሩስ በጦርነቱ በቀጥታ ባትሳተፍም የሩስያ ወታደሮች ግዛቷን ተጠቅመው ወረራውን እንዲጀምሩ ፈቅዳለች።

ሚንስክ "በልዩ ወታደራዊ ዘመቻው" ድጋፏን እንድታጠናክር ከሞስኮ ግፊት እየበረታባት ነው።

ሚኒስክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ግን ሪፖርቶቹን “ፍፁም የማይረቡ፣ መሠረተ ቢስ የፈጠራ ወሬ” ሲሉ አጣጥለውታል።

ፕሬዝዳንት ፑቲን ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፕሬዚዳንት ሉካሼንኮ ጋር ለመነጋገር ወደ ሚንስክ አቅንተዋል።

ከሁለት ሰዓት በላይ የፈጀው ስብሰባው "የሥራ ጉብኝት" ተብሎ ተገልጿል።

የጋራ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ፕሬዝዳንት ፑቲን እንደተናገሩት ሩሲያ ማንንም “መሳብ” አትፈልግም። "ጠላቶች" ያሏቸውም ሩሲያ ከቤላሩስ ጋር ያላትን ውህደት ለማስቆም እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ሰኞ ዕለት እንደተናገሩት የፑቲን መግለጫ ዩክሬንን ለማዋሃድ ከመፈለጋቸው አንጻር "ትልቅ ስላቅ" ነው ብለውታል።