ሴት ተማሪዎች ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ ለመከልከል የተመረዙባት ኢራን

ታትሟል

በኢራን ቢያንስ 650 ሴት ተማሪዎች መመረዛቸውን ቢቢሲ አረጋግጧል።

አንድ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣንም ሴት ተማሪዎቹ ሆን ተብለው ኢላማ መደረጋቸውንም አምነዋል።

ምንም እንኳን በዚህ ድርጊት ሕይወት ባያልፍም፣ በርካቶች ባጋጠማቸው የመተንፈሻ አካላት ችግር፣ ማቅለሽለሽ እና ድካም ምክንያት ወደ ሆስፒታል ገብተዋል።

“አንዳንድ ሰዎች ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለይም የሴቶች ትምህርት ቤት እንዲዘጉ እንደሚፈልጉ ግልጽ እየሆነ መጥቷል” በማለት የኢራን ምክትል የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዩኔስ ፓናሂ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

እስካሁን ከኢራን መንግሥት በኩል የተሰጠው ይፋዊ መግለጫ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተማሪዎቹ መመረዛቸውን በተመለከተ የወንጀል ምርመራ መከፈቱን እና ሆን ተብሎ የተፈጸመ ሊሆን ይችላል ማለታቸው ብቻ ነው።

በባለፉት ሦስት ወራት ሴት ተማሪዎቹ ከመታመማቸው በፊት የመንደሪን ወይም የበሰሰበ ዓሳ እንደሸተታቸው ሪፖርት አድርገዋል።

“ጥቅም ላይ የዋሉት ኬሚካሎች በገበያ ላይ ያሉ ወይም በከፍተኛ ደረጃቸውን የጠበቁ አይደሉም” ብለዋል ዶ/ር ፓናሂ።

“ተማሪዎቹ ከፍተኛ ህክምና አያስፈልጋቸውም እናም መረጋጋት ያስፈልጋል” ሲሉም ተናግረዋል።

ዶክተሩ የሰጡት መግለጫ የተሳሳተ ትርጉም ተሰጥቶታል ሲሉም ተናግረዋል።

ለተማሪዎቹ መመረዝ ጥፋተኛው ማን እንደሆነ ይፋ ባልሆነበት ወቅት የሕዝብ ቁጣን እንዴት ማስተናገድ ይቻላል የሚለውንም ማስተባበላቸውን ያሳየ ነው ተብሏል።

በጥብቅ ሃይማኖተኝነት የምትታወቀው የቆም ከተማ የተማሪዎቹ መመረዝ ማዕከል ብትሆንም፣ በኢራን ውስጥ እስከ ስምንት በሚደርሱ ከተሞች ላይ ተመሳሳይ መመረዝ በተማሪዎቹ ላይ ተፈጽሟል ተብሏል።

በዚህም የተነሳ በርካቶች ቁጣቸውንም እያሰሙ ነው ተብሏል።

ሴት ተማሪዎቹ መጀመሪያ የተመረዙት ኅዳር አጋማሽ ላይ ነው። በቆም ከተማ በሚገኘው የኑር ቴክኒክ ትምህርት ቤት 18 ተማሪዎች የመመረዝ ምልክት ካሳዩ በኋላ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።

ከዚያ በኋላም በግዛቲቷ ከ10 በላይ የሴት ትምህርት ቤቶች ኢላማ ሆነዋል።

በየካቲት ወር አጋማሽ ቢያንስ 100 የሚሆኑ ሰዎች በቆም ከተማ አስተዳዳሪ ቢሮ ውጪ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

“የልጆቼን ደኅንነት የማስጠበቅ ግዴታ አለብህ! ሁለት ሴት ልጆች አሉኝ” ሲሉም አንድ አባት በማኅበራዊ ሚዲያ በሰፊው በተሰራጨ ቪዲዮ ላይ ሲጮሁም ይሰማል።

“ሁለት ሴት ልጆች….. እናም ብቸኛው ማድረግ የምችለው ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ መከልከል ነው” ሲሉም ተሰምተዋል።

“ይህ ጦርነት ነው!” በማለት በተቃውሞ ሰልፉ ላይ የምትናገር ሴት ትደመጣለች።

“በቆም በሚገኘው የሴቶች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይህንን እያደረጉ ያሉት ሴቶች ቤት እንድንቀመጥ ለማስገደድ ነው። እኛ ሴቶች ቤታችን እንድንቀመጥ ይፈልጋሉ” ብላለች።

አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው ከተመረዙ በኋላ ለሳምንታት ታመው እንደነበር ገልጸዋል።

በሆስፒታል የተቀረጸ ሌላ ቪዲዮ በአልጋ ላይ ታማ ያለች ታዳጊ እናቷ ደግፈዋት ታይተዋል።

“ለውድ እናቶች፣ እኔም እናት ነኝ ልጄም በሆስፒታል አልጋ ላይ ናት እግሮቿ መንቀሳቀስ አይችሉም” በማለት በጭንቀት የተዋጡት እናት ተናግረዋል።

“እግሯን ብነካትም፣ ብቆነጥጣትም ምንም አይሰማትም። እባካችሁ ልጆቻችሁን ወደ ትምህርት ቤት እንዳትልኩ” ብለዋል።

የሃይማኖት ማዕከል የሆነችው ከተማ

ጥቃቱ ያተኮረው የእስላማዊ ሪፐብሊክ የጀርባ አጥንት በሆኑት የሺዓ እስልምና ሃይማኖት መሪዎች መኖሪያ በሆነችው ቆም ከተማ ነው።

ኩርዳዊቷ ወጣት ማህሳ አሚኒ ከወራት በፊት የራስ መሸፈኛዋን በአግባቡ አልለበሰችም በሚል በሞራል ፖሊሶች ከተገደለች በኋላ የሃይማኖት መሪዎቹ ሥልጣን ጥያቄ ውሰጥ ገብቷል። ወጣቶችም እየተገዳደሯቸው ይገኛሉ።

በተማሪዎቹ ላይ እየተፈጸመ ያለው የመርዝ ጥቃት በኢራን የተካሄደው መጠነ ሰፊ ፀረ- መንግሥት ዘመቻ አጸፋዊ ምላሽ እንደሆነ አንዳንዶች ያምናሉ። ሴት ተማሪዎች የፀጉር መሸፈኛቸውን እያወለቁ ሲወረውሩም የሚያሳዩ ምስሎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ወጥተዋል።

በርካቶችም በሌላ መልኩ እነዚህ ጥቃቶች ጽንፈኞቹ የአፍጋኒስታኑ ታሊባን እና የናይጄሪያውን ቦኮ ሃራምን ተግባር ለመቅዳት በሚፈልጉ ጽንፈኞች የተደረገ እንደሆነ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ወላጆችን በማስፈራራት ሴት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዳይልኩ ማድረግ የሚል ስትራቴጂ ነው።

“ቦኮ ሃራም ኢራን ገባ እንዴ?” ሲሉም የቀድሞው የኢራን ምክትል ፕሬዝዳንት መሐመድ አሊ አብታሂ በኢንስታግራም ገጻቸው ላይ ጠይቀዋል።

የለውጥ አራማጁ ፖለቲከኛ “አክራሪዎች መንግሥትን እና ሃይማኖትን ለራሳቸው በሚመች በኩል ይተረጉሙታል” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

የኢራን መንግሥት አስገዳጅ የሆነውን ፀጉርን መሸፈን እና ሌሎች ገደቦችን በሴቶች ላይ ጥሏል በሚል ትችት የሚቀርብበት ቢሆን፣ በርካታ ሴት ተማሪዎች ዩኒቨርስቲ ገብተዋል በማለት ወቀሳዎቹን ሲያጣጥል ቆይቷል።

ነገር ግን ሴት ተማሪዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዲያጠናቀቁ ዕድል ካላገኙ ኮሌጅ ባዶ ተስፋ ይሆናል።

ከቆም ከተማ አስተዳዳሪ ጋር በተደረገው ስብሰባ ሁለት ጊዜ መመረዟን አንዲት ተማሪ መናገሯን ተከትሎ አንዳንድ የባለሥልጣናት መግለጫዎች ምን ያህል አሳሳች እንደሆኑ ያሳያል ተብሏል።

“እነሱ (ባለሥልጣናት) ሁሉም ነገር ጥሩ እንደሆነ፤ ምርመራችንን ጨርሰናል ብለውናል። ነገር ግን አባቴ ትምህርት ቤቱን ሲጠይቅ የደኅንነት ካሜራው (ሲሲሲቲቪው) ስለማይሰራ ይህንን መመርመር አንችልም ሲሉም ነግረውታል” ስትል በስብሰባው ላይ ተናግራለች።

“እና እሁድ ለሁለተኛ ጊዜ በተመረዝኩበት ጊዜ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር የልብ ህመም አለባት ለዚህም ነው ሆስፒታል የገባችው ብሎ ተናገረ። እኔ ግን ምንም አይነት የልብ ህመም የለኝም” ብላለች።