ከእጮኛዋ የተለያየችው ኡጋንዳዊት ካሳ እንድትከፍለው ተፈረደባት

ታትሟል

ከእጮኛዋ ጋር ባለመግባባት የተለያየችው ኡጋንዳዊት ላደረሰችበት ‘ሥነ ልቦናዊ ስብራት’ ካሳ እንድትከፍለው በፍርድ ቤት ታዘዘች።

በኡጋንዳ፣ ካኑንጉ የሚገኘው ፍርድ ቤት እንዳለው ሪቻርድ ቱሚውኔ የተባለው ግለሰብ እጮኛው ሲለያዩ አብረው በነበሩበት ጊዜ የሕግ ትምህርቷን እንድትከታተል የከፈለውን ገንዘብ እንድትመለስ ታዛለች።

በዚህም እጮኛው ፎርቹኔት ካያሪኩንዳ ለትምህርቷ የወጣውን 9.4 ሚሊዮን የኡጋንዳ ሽልንግ (2,550 ዶላር) እንዲሁም ለፍርድ ቤት ያወጣውን ወጪ ጨምራ ካሳ እንድትከፍል ተወስኖባታል።

ዳኛ አሳናሲዮ ሙኮቢ ገንዘቡ እንዲከፈል የወሰኑት ግለሰቧ ከእጮኛዋ ጋር ከአራት ዓመት ቆይታ በኋላ ለመለያየት በመወሰኗ ነው።

በዚህም ፎርቹኔት ካያሪኩንዳ ለእጮኛዋ የገባችውን ቃል ስላልጠበቀች እሷን ለማስተማር ያወጣው ገንዘብ ተሰልቶ ከተጨማሪ ወጪው ጋር እንድትመልስለት ውሳኔው እንደተሰጠም ተገልጿል።

ፎርቹኔት ለመለያየታቸው ምክንያቱ እጮኛዋ ከእሷ በዕድሜ ስለሚበልጥ ቤተሰቦቿ በዕድሜ የገፋ ሰው እንዳታገባ እንደነገሯት ገልጻ የውሳኔዋን ምክንያት ለፍርድ ቤቱ ለማስረዳት ሞክራ ነበር።

ግለሰቡ እሷን ለመደገፍ “ገንዘብ ከማውጣቱ አስቀድማ ግንኙነታቸው ሲጀመር የመቀጠል ፍላጎት እንደሌላት” መግለጽ ትችል እንደነበረ በፍርድ ቤቱ ተገልጿል።

ነገር ግን ችሎቱ ያቀረበችው መከራከሪያ “ምክንያታዊ ያልሆነ፣ ማጭበርበር እና ማታለል ነው” በማለት ውድቅ በማድረግ ውሳኔ ሰጥቷል።

ነገር ግንፎርቹኔት በፍርድ ቤቱ የተሰጠባትን ብይን ለማስቀልበስ ይግባኝ ትጠይቅ እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም።

አስተያየት ሰጪዎች እንዳሉት፣ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የተዛባ ነው። ምክንያቱም ትዳር ያልመሠረቱ እጮኛሞች የሚገቡት ቃል የሕግ ከለላ የለውም ሲሉ ውሳኔውን ተችተዋል።

የሴቶች መብት ተሟጋች ተቋም የምትሠራው ሺላ ክዋማራ እንደምትለው፣ ወንዶች ሴቶች ያገቡናል ብለው ገንዘብ የሚሰጡባቸው ጊዜያት አሉ።