የሰውነት ክፍላቸውን የሚለግሱ ታራሚዎች የእስር ዘመን እንዲቀነስ ሐሳብ ቀረበ

የማሳቹሴትስ ግዛት ይህን አወዛጋቢ ረቂቅ ያጸድቃል ተብሎ አይጠበቅም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የማሳቹሴትስ ግዛት ይህን አወዛጋቢ ረቂቅ ያጸድቃል ተብሎ አይጠበቅም
ታትሟል

በአሜሪካ ማሳቹሴትስ ግዛት የሰውነት ክፍላቸውን አልያም የአጥንት መቅኔያቸውን ወረፋ ለሚጠብቁ ሕመምተኞች የሚለግሱ ታራሚዎች የእስር ዘመናቸው እንዲቀነስላቸው ምክረ ሐሳብ ቀረበ።

እነዚህ ታራሚዎች ይህ በጎ ተግባር ከፈጸሙ ከአንድ ዓመት ያልበለጠ የእስር ቅነሳን ያገኛሉ።

ሁለት ዲሞክራት የሕግ አውጪዎች ይህ ረቂቅ ለእስረኞች የተሻለ ዕድል የሚሰጥ ነው ብለዋል።

የረቂቁ ተቺዎች ግን ይህ ሐሳብ ሥነ ምግባርን የጣሰ ነው፤ ታራሚዎችም ያሉበትን ችግር መጠቀሚያ የሚያደርግ ነው፤ ተስፋ በማጣት የማይፈልጉትን ነገር እንዲያደርጉ የሚያበረታታ ነው ብለዋል።

በአሜሪካ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ታራሚዎች የሰውነት አካልን እንዲለግሱ የሚፈቀድላቸው ተቀባዩ የቅርብ ቤተሰብ ከሆነ ብቻ ነው።

ይህ ረቂቅ የአካል ልገሳ ማዕከላትን በማረሚያ ቤቶች የማቋቋም ትልምን የያዘ ነው።

በአሁኑ ጊዜ በማሳቹሴትስ ግዛት ከ5 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ለጋሽ እየጠበቁ ይገኛሉ።

ረቂቁ አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴ በየማረሚያ ቤቶች እስረኛ ለጋሾች የትኛውን የአካል ክፍል ለመለገስ እንደፈቀዱ መዝግቦ የእስር ጊዜያቸውን በምን ያህል መቀነስ እንዳለበት እንዲወስን ምክረ ሐሳብ ያቀርባል።

ለጋሽ ታራሚዎች ለሚለግሱት የአካል ክፍል ምንም ዓይነት ገንዘብ ክፍያ አይፈጸምላቸውም።

የማሳቹሴትስ ግዛት የምክር ቤት አባል ካርሎስ ጎንዛሌዝ ይህ ምክረ ሐሳብ ሕይወታቸውን ለማቆየት እያጣጣሩ ላሉ የግዛቲቱን ነዋሪዎች ሕይወት አድን ለጋሾችን ቁጥር በመጨመር ተስፋቸውን የሚጨምር ይሆናል።

ካርሎስ ጎንዛሌዝ ለቦስተን ሚዲያ እንደተናገሩት አንድ ወዳጃቸው ደረጃ-4 የኩላሊት ሕመም ደርሶባቸው ለጋሽ በመጠባበቅ ላይ ናቸው። ይህ አጋጣሚም ነው ምክረ ሐሳቡን እንዲደግፉ ያደረጋቸው።

“ባልንጀራዬን እወደዋለሁ፤ ሕይወቱ እንድትቀጥል እጸልይለታለሁ፤ አሁን የቀረበው ረቂቅ የእሱንም ሆነ በሕይወትና በሞት መሀል ያሉ ሌሎችን ሰዎች የሚታደግ ይሆናል” ሲሉ ድጋፍ ሰጥተዋል።

የሐሳቡ ተቺዎች ታራሚዎችን ከሰው በታች የሚያደርግ ነው ሲሉ ረቂቁን ወርፈውታል።

ኬቨን ሪንግ የተባሉ የአንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መሪ ረቂቁን ክፉኛ ተችተውታል።

“ታራሚዎች ከሰው በታች ዝቅ አድርጎ ከማየት የመጣ ነው፤ ነጻ ለመውጣት ከፍተኛ ጉጉት ስላላቸው ያን ደካማ ጎናቸውን ለራስ ጥቅም ማዋል አሳፋሪ ነው። ታራሚዎች ልክ እንደኛው ሰው እንደሆኑ ለምን ተዘነጋን?” ብለዋል።

በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች ይህ ረቂቅ ይጸድቃል ብለው አያስቡም።