የሶሪያ መንግሥት የቢቢሲን የሥራ ፈቃድ ሰረዘ

ታትሟል

የሶሪያ መንግሥት የቢቢሲ ዘገባ “ሚዛናዊ ያልሆነና አሳሳች ነው” በሚል የድርጅቱን የሥራ ፈቃድ ሰረዘ።

የሶሪያ ኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር እንዳለው የሚድያ ተቋሙ “ሙያዊ በሆነ መንገድ” ሥራውን መከወን አልቻለም።

በቅርቡ ቢቢሲ የሠራው አንድ ዘገባ፤ ካፕራጎን የተሰኘ መድኃኒት ንግድ ከሶሪያው ፕሬዝደንት በሻር አል-አሳድ ቤተሰብ ጋር ግንኙነት እንዳለው ያሳያል።

ይህ አምፌታሚን የተሰኘው የመድኃኒት ዓይነት ኃይል ሰጪ ንጥረ-ነገሮች አዝሏል።

ቢቢሲ ዘገባው ሚዛናዊ እና ገለልተኛ ነው ሲል ይገልጣል።

“በፖለቲካው ዙሪያ ያሉ ሁሉን አነጋግረን እውነተኛ ዘገባ ሠርተናል” ይላሉ የቢቢሲ ቃል አቀባይ።

ባለፈው ዓመት የታተመው ይህ ዘገባ በቢቢሲ አረብኛው ክፍል የተሰናዳ ነው።

በካፕታጎን ንግድ ዙሪያ የሶሪያ ጦር ሠራዊት መሪዎች እና የአሳድ ቤተሰብ እጃቸው እንዳለበት ዘገባው ያሳያል።

ካፕታገን እጅግ በጣም ኃይለኛ ሱስ ውስጥ የሚከት መድኃኒት ሲሆን የሶሪያ መንግሥት ከዚህ ቀደም በዚህ መድኃኒት ንግድ እጄ የለበትም ሲል ማስተባበሉ አይዘነጋም።

ነገር ግን የዩናይትድ ስቴትስ፣ ዩኬ እና የአውሮፓ ሕብረት በዚህ አይስማሙም።

ይልቁንስ የሶሪያ መንግሥት ይሄን መድኃኒት አምርቶ ወደ ውጭ እየላከ ነው፤ ይህን የሚያደርጉት የአሳድ ቤተሰብ አባላት ናቸው ሲሉ ይወቅሳሉ።

የሶሪያ መንግሥት የቢቢሲ ፈቃድ ሲሰርዝ ስለመድኃኒቱ የሠራውን ዘገባ አልጠቀሰም።

ነገር ግን የሶሪያ እርስ በርስ ጦርነት በፈረንጆቹ 2011 ከተጀመረ ወዲህ ቢቢሲ በአንዳንድ ዘገባዎቹ “ሚዛን የሳተና ሐሰተኛ መረጃ” ሲያሰራጭ ቆይቷል ብሏል።

መግለጫው አክሎ ቢቢሲ “ከአንድም ሁለት ሶስቴ” ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠው ገልጧል።

“ቢሆንም ሚድያው ከመግለጫዎች፣ አሸባሪ ድርጅቶችና ለሶሪያ ክፉ ከሚያስቡ ምንጮች በሚያገኘው መረጃ አሳሳች ዘገባዎቹን መሥራት ቀጥሎበታል።”

ቢቢሲ “ሚዛናዊ ዘገባ እና መረጃ ለአረብኛ ተናጋሪ ተከታዮቻችን ማድረስ እንቀጥላለን” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።

ድንበር አልባው የሪፖርተሮች ማሕበር ሶሪያን በፕረስ ነፃነት ከ180 ሃገራት 175ኛ ላይ ያስቀምጣታል።

እንዲህም ሆኖ በጦርነት የታመሰችው ሶሪያ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን የሥራ ፈቃድ የመሰረዝ ልምድ የላትም።