ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአውስትራሊያ የሠርግ ታዳሚዎችን ያሳፈረ አውቶብስ ተገልብጦ ቢያንስ 10 ሰዎች ሞቱ
በአውስትራሊያ የሠርግ ታዳሚዎችን ያሳፈረ አውቶብስ ተገልብጦ ቢያንስ 10 ሰዎች ሲሞቱ ሌሎች 25 ሰዎች ተጎድተው ሆስፒታል ገቡ።
ሀንተር ቫሊ በተባለ አካባቢ ሠርግ ታድመው የሚመለሱ ሰዎች የጫነው አውቶብስ ከተገለበጠ በኋላ ፖሊስ የ58 ዓመቱን አሽከርካሪ በቁጥጥር ሥር አውሏል።
የአውቶብሱ አሽከርካሪ ሞት ባስከተለ አደገኛ አነዳድ 10 ክሶች እንደሚመሠረቱበት ተገልጿል።
አካባቢው በወይን አቅርቦቱ ስለሚታወቅ ቱሪስቶች ያዘወትሩታል።
ሙሽሮቹ አደጋው በደረሰበት አውቶብሱ ውስጥ ያልነበሩ ሲሆን፣ የሞቱትን ሰዎች ማንነት ለመለየት እየተሠራ እንደሆነ ተገልጿል።
የፖሊስ ኮሚሽነር ካረን ዌብ አደጋው የተከሰተበት ቦታ “ወንጀል የተፈጸመበት ነው። ምርመራ እያደረግን ነው። አሻራ መርማሪዎች አሰማርተናል። የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችም አሉ” ብለዋል።
አደጋው የተከሰተው በአካባቢው ከፍተኛ ጭጋግ በነበረበት ወቅት እንደነበር ገልጸዋል።
አውቶብሱ የተገለበጠው ሲጓዝበት በነበረው አውራ ጎዳና ላይ ያለ አደባባይ አልፎ ሊታጠፍ ሲል ነው።
ተባባሪ የፖሊስ ኮሚሽነር ትሬሲ ቻፕማን እንዳሉት ሠርገኞቹ ወደ ማረፊያ ቦታቸው እየተጓዙ ነበር። ከአደጋው ከተረፉት ሁለቱ በአውሮፕላን መወሰዳቸውንም ገልጸዋል።
ቢያንስ አንደኛው ለሕይወት አስጊ ሁኔታ ላይ እንዳሉ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዝ “በጣም የከፋ ነው። በጣም ያሳዝናል። ያን በመሰለ ቦታ የተካሄ ውብ ሥነ ሥርዓት በዚህ አሳዛኝ ሁኔታ መጠናቀቁ ያሳዝናል” ብለዋል።
ሙሽሮች ለእንግዶቻቸው ደኅንነት ሲሉ አውቶብስ እንደተከራዩ እና የተፈጠረው አደጋ ግን እጅግ እንደሚያሳዝንም ገልጸዋል።
“ለማሰብ የሚከብድ ነው አደጋው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
በአደጋው ከተጎዱት የተወሰኑት ጆን ሀንተር በሚባል ሆስፒታል ሲገኙ፣ ሌሎች ደግሞ ወደ ሲድኒ ከተማ እንደተወሰዱ ተናግረዋል።
የአካባቢው አገረ ገዢ ክሪስ ሚንስ ይህ ሁሉ ሕይወት መጥፋቱ “ልብ ይሰብራል። በፀሎታችን እናስባቸዋልን” ብለዋል።
አንድ የሠርጉ ታዳሚ ቀኑ በጥሩ ሁኔታ ሄዶ ማለቂያው ሐዘን መሆኑ እንደሚያስከፋ ገልጸዋል።