የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በስልክ ተወያዩ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እና ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ
የምስሉ መግለጫ, የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እና ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር የስልክ ውይይት ማድረጋቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ውይይቱ ዛሬ ማክሰኞ ሐምሌ 15/2017 ዓ.ም. መደረጉን ያመለከተው የቃል አቀባይ ጽህፈት ቤቱ በሁለቱ አገራት እና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ባለሥልጣናቱ መነጋጋራቸውን ጠቅሷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት እና የምጣኔ ሃብት ዕድገት ላይ መነጋገራቸው ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ማርኮ ሩቢዮ በቀጣናው የውይይትን እና የመረጋጋት አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በነበራቸው የስልክ ንግግር ወቅት ማንሳታቸውን መሥሪያ ቤታቸው አስታውቋል።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በስልክ የተወያዩት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው አለመግባባት እየተባባሰ በሄደበት እና ሁለቱ አገራት የሚያሰሙት መካሰስ ወደ ግጭት ሊያመራ ይችላል የሚል ስጋት ባየለበት ጊዜ ነው።

በተጨማሪም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ ግንባታውን አጠናቅቃ ልታስመርቀው የተቃረበችውን ታላቁን የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ አወዛጋቢ ንግግር በተደጋጋሚ ማድጋቻው እያነጋገረ ባለበት ጊዜ ነው።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባለፉት ሳምንታት የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ባደረጓቸው ንግግሮች የአባይን ውሃ የሚያስቆም እና ግብፅን የሚጎዳ አድርገው በአሉታዊ መልኩ የገለጹት ሲሆን፣ በተጨማሪም ለግድቡ ግንባታ አሜሪካ ድጋፍ ማድረጓን በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

ይህም ግንባታው አስራ አራት ዓመታት የፈጀው በአፍሪካ ግዙፉ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ወጪው በኢትዮጵያውያን የተሸፈነ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ ሲገልጽ ከነበረው ጋር የሚቃረን ነው።

የፕሬዝዳንት ትራምፕን ንግግር በተመለከተ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ምንም ዓይነት ምላሽ ሳይሰጥ ቆይቶ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሕዝብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ለዚሁ ምላሽ በሚመስል ሁኔታ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

ጽህፈት ቤቱ እንዳለው ታላቁ ሕዳሴ ግድብ መገንባት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ከአገር ውስጥ እና በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአጠቃላይ ከ23.6 ቢሊዮን ብር በላይ ተሰብስቦ ለግድቡ ግንባታ መዋሉን እና የግንብታው ወጪ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያውያን የተሸፈነ መሆኑን ገልጿል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በስልክ የተወያዩት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ መሥሪያ ቤት አሜሪካ ለውጭ አገራት ዜጎች በምትሰጠው ቪዛ ላይ ማስተካከያ እያደረገ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያውያን በሚሰጠው ቪዛ ላይ ለውጥ ማድረጉ ይታወሳል።

በዚህም መሠረት ከዚህ ደቀም ወደ አሜሪካ ለሚገቡ ኢትዮጵያውያን የሚሰጠው በተደጋጋሚ ለመግባት የሚያስችላው የሁለት ዓመታት ቪዛ ቀርቶ ለአንድ ጊዜ መግቢያ ብቻ እና ለሦስት ወራት የሚያገለግል እንዲሆን መደረጉ ይታወሳል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በተጨማሪም የኢትዮጵያን የምጣኔ ሃብት የለውጥ እርምጃዎችን ማድነቃቸውን እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ የአሜሪካንን ንግድ እና ኢንቨስትመን ዕድሎችን ለማስፋት አቅም መኖሩን በውይይቱ ላይ ማንሳታቸው ተጠቅሷል።