ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የትራምፕ አስተዳደር ከሕክምና ምርምር ወጪዎች 4 ቢሊዮን ዶላር ለመቀነስ ወሰነ
የትራምፕ አስተዳደር አላስፈላጊ ወጪ ቅነሳ በሚል በጀመረው ዘመቻ ከባዮሜዲካል ምርምር ወጪ በትንሹ 4 ቢሊዮን ዶላር ለማዳን ወሰነ።
ለሕክምና ሳይንስ ምርምር ከሚወጣው ወጪ 4 ቢሊዮን ዶላር የሚቀነሰው በዋናነት የሥራ ማስኬጃ ወጪዎች ላይ ነው።
ሳይንቲስቶች ይህ ውሳኔ የሳይንስና ምርምር ዓለምን ክፉኛ ይጎዳል እያሉ ነው።
የብሔራዊ ጤና ኢንስቲትዩት ዐርብ ባወጣው መግለጫ ከምርምር ጋር ቀጥታ ያልሆኑ ወጪዎች ለምሳሌ የኪራይ፣ የቁሳቁስ፣ የሕንጻ ግንባታና ሌሎች ሥራ ማስኬጃዎች በዚህ ውሳኔ ተካተዋል።
"አሜሪካ ምርጥ የሕክምና ምርምር ማዕከል መዳረሻ መሆን አለባት" የሚለው መግለጫው ከመንግሥት የሚገኙ ድጎማዎችና ችሮታዎች በቀጥታ ለሳይንስና ምርምሩ ብቻ መዋል አለባቸው ብሏል።
በርካታ ገንዘብ በሥራ ማስኬጃ ወጪ እንደሚባክንም አመላክቷል።
ከሰኞ ጀምሮ ተግባራዊ በሚሆነው በዚህ ወጪ ቅነሳ በትንሹ 4 ቢሊዯን ዶላር ለማዳን ታቅዷል።
በትራምፕ አስተዳደር አዲስ የተመሠረተውና ቢሊየነሩ ኤሎን መስክ የሚመሩት "የመንግሥት አስተዳደር ተሳልጦ ጽሕፈት ቤት" ነው ይህን ወጪ ቅነሳ የሚመራው።
ይህ ጽሕፈት ቤት በአሜሪካ ትልቁ የተራድኦ መሥሪያ ቤት፣ ዩኤስኤይድ ላይ በወሰደው እርምጃ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ቀወስ መፍጠሩ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ በዚህ ድርጅት ከዓለም ትልቁን እርዳታ ከሚያገኙ አገሮች ከፊት ተሰልፋ ነበር።
ቢሊየነሩ ኤሎን መስክ የሚመሩት የዚህ ጽሕፈት ቤት ዋንኛ ተግባር የመንግሥት ወጪዎችን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ነው።
የሕክምና ምርምር ድጎማን በተመለከተ ኤለን መስክ በኤክስ ገጻቸው እንደተቹት ብዙዎቹ ዩኒቨርስቲዎች ለጥናትና ምርምር ከሚያገኙት ገንዘብ 60 ከመቶ የሚሆነውን ለሥራ ማስኬጃ እንጂ ለምርምር አይጠቀሙበትም።
"ይሄ ደግሞ እልም ያለ ዘረፋ ነው" ብለዋል ቢሊየነሩ መስክ።
ሳይንቲስቶች በበኩላቸው ይህ ውሳኔ 'የሳይንስና ምርምርን በብርቱ ይጎዳዋል" ብለዋል።
የአሜሪካ የሜዲካል ኮሌጅ ማኅበር በበኩሉ ውሳኔውን በመቃወም መግለጫ አውጥቷል። በዚህ መግለጫው "ሥራ ማስኬጃ ወጪዎች ናቸው ምርምሩ እንዲሰምር የሚያደርጉት" ብሏል።
ይህ ወጪ የማዳን እርምጃ "አዳዲስ ምርምሮችን የሚያንጓትት፣ በሕምናው አዲስ ግኝት ለማየት በጉጉት የሚጠብቁ ቤተሰቦችንና ዜጎችን ስሜት የሚጎዳ" ብሎታል።
በስታንፈርድ ዩኒቨርስቲ የካንሰርና የጨረር ሕክምና ተመራማሪ አኑሻ ካልባሲ ይህን ውሳኔ ተከትሎ በሰጡት አስተያየት ለምርምሩ በሚሰጥ ችሮታ ለሥራ ማስኬጃ የሚወጣው ወጪ አላስፈላጊ አይደለም ብለዋል።
"መብራቱ፣ ቬንትሌተሩ በላብራቶሪው ውስጥ ያሉ ቁሳቁሶች በሙሉ እኛን ተመራማሪዎቹ ሥራውን እንድንቀጥል ነው የሚያደርጉን፣ የሚቀጠሩት አጋዦቻችን እኛ ተመራማሪዎች ትኩረታችን ጥናቱ ላይ ብቻ እንድናደርግ ያስችሉናል።"
የአሜሪካ የትምርት ካውንስል በበኩሉ ውሳኔውን ተቃውሞ ባወጣው መግለጫ የሥራ ማስኬጃ የምርምር ወጪዎች 'አላስፈላጊ ወጪ ሊባሉ አይችሉም" ብለዋል።
ዘመናዊ ላቦራቶሪዎች እንዲኖሩ የተቻለው በዚህ የገንዘብ ድጋፍ ነው። አሜሪካ በምርምር ከዓለም አንደኛ እንድትሆን ይህ ገንዘብ የግድ ነው ብሏል።
የተቋሙ መሪ ቴድ ሚችል ለዋሺንግተን ፖስት እንደተናገሩት ዜናው ከመሰማቱ አንዳንድ የምርምር ተቋማት ከአሁኑ ሥራቸውን ማቋረጥ ጀምረዋል።
እርሳቸው የሚመሩት የትምህርት ካውንስል የኤለን መስክ ውሳኔን በመቃወም ፍርድ ቤት ክስ እንደሚመሰርቱ ተናግረዋል።