''የዩክሬን መልሶ ማጥቃት ሊያበቃ የቀሩት 30 ቀናት ናቸው'' አሜሪካዊ ጄነራል

ታትሟል

አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን ዩክሬን የአየር ሁኔታው ከመቀየሩ እና የመልሶ ማጥቃት ስልቷን ከማስተጓጎሉ በፊት ለመዋጋት ያላት ከ30 የያይበልጡ ቀናት ብቻ እንደሆኑ ገለፁ።

ጄነራል ማርክ ሚሊ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከ30 ቀናት በኋላ ለዩሬናውያን የጦር ስልት ቀዝቃዛው የአየር ሁኔታ እንቅፋት ይሆናል።

ጄነራሉ አክለውም ማጥቃቱ ከተጠበቀው በላይ ዝግ ብሎ እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል።

አክለውም “አሁንም ከባድ ውግያ እየተካሄደ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

“ምንም እንኳ አዝጋሚ ቢሆንም ዩክሬናውያን በአውደ ውግያቸው ወጥ አቋም እያሳዩ ቀጥለዋል።”

ጄነራሉ የዩክሬናውያን መልሶ ማጥቃት ከሽፏል ለማለት አሁን ጊዜው አለመሆኑን ገልጸው፣ “በሩሲያ የጦር ቀጠናዎች ወጥ በሆነ መልኩ እየተዋጉ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

“አሁንም ቢሆን የማይናቅ ጊዜ አለ፤ ምናልባት ከ30 እስከ 45 ቀናት ድረስ ለመዋጋት የሚያስችል የአየር ሁኔታ አለ። ስለዚህ ዩክሬናውያን ገና አልተረቱም'' ብለዋል።

“ገና የሚካሄዱ ውግያዎች አሉ. . . ሊቀዳጁ ከሚፈልጉት ድል አንጻር ገና የሚያካሄዱት ያልተጠናቀቁ ጦርነቶች አሉባቸው።”

የኪየቭ መልሶ ማጥቃት በሩስያ የተያዙባትን ግዛቶች ነጻ ማውጣት አልሞ በበጋው ወራት የተጀመረ ሲሆን እስካሁን ድረስ የተገኘው ድል አነስተኛ መሆኑ እየተነገረ ነው።

ነገር ግን የዩክሬን ጦር ጄነራሎች በደቡብ በኩል በሩስያ የጦር ግንባር የማይናቅ ድል እንደተቀዳጁ ይናገራሉ።

“ጦርነቱ ሲጀመር ረዥም፣ዝግ ያለ እና አስቸጋሪ፣ ከፍተኛ መስዋዕትነት የሚከፈልበት እንደሚሆን ተናግሬ ነበር። የሆነውም ያ ነው” ብለዋል አሜሪካዊው ጄነራል ለቢቢሲ።

የዩኬ ጦር ጄነራል የሆኑት አድሚራል ሰር ቶኒ ራዳኪን በበኩላቸው “ዩክሬን እያሸነፈች፣ ሩስያ ደግሞ እየተሸነፈች ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ለዚያ ደግሞ ምክንያቱ የሩስያ አላማ ዩክሬንን መውረር እና በቁጥጥሯ ስር ማድረግ ነበር” ብለዋል።

“ያ ደግሞ አልሆነም። በጭራሽ ሊሆንም የሚችል አይደለም። ለዚያ ነው ዩክሬን እያሸነፈች ያለችው።”

አክለውም ዩክሬን በአውደ ውግያዎቹ ግዛቶቿን በማስመለስ ረገድ ውጤታማ መሆኗን ገልጸው እስካሁን ሩስያ ይዛ ከነበረው 50 በመቶ ማስመለስ መቻሏን ተናግረዋል።

የዩክሬን ጦር ድል በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ላይ የተመሠረተ ጭምር መሆኑን ሲናገሩ “የኢኮኖሚ እንዲሁም የዲፕሎማቲክ ጫናው ሩስያ ከፍተኛ መስዋዕትነት አንድትከፍል አድርጓታል።” ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እያለ ቭላድሚር ፑቲን ከሰሜን ኮርያ ጋር የፈጠሩት ወዳጅነት “በተስፋ መቁረጥ ውስጥ መሆናቸውን “ ነው ሲሉ ራዳኪን ተናግረዋል።

የሁለቱ አገራት ወዳጅነት የሚያሳየው ሩስያ ምን ያህል ጥቂት ወዳጅ ብቻ እንደቀራት ነው ሲሉ ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

የሰሜን ኮርያው ፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡን በዚህ ወር ሩስያን ለመጎብኘት እና ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ተገናኝተው በጦር መሳርያ ዙርያ ለመነጋገር ቀጠሮ ይዘዋል።

ሁለቱ መሪዎች ተገናኝተው ሩስያ በዩክሬን ለምታካሄደው ጦርነት የጦር መሣርያ ድጋፍ የምታገኝበት እቅድ ላይ ይነጋገራሉ።

ዋሺንግተን እና ሶል በበኩላቸው ሰሜን ኮርያ በልዋጩ የጦር መሣርያ ስምምነት አግኝታ ሁለቱ አገራት በእስያ ያላቸው ወታደራዊ ትብብር ይጨምራል ሲሉ ሰግተዋል።