በአሜሪካ አላስካ ግዛት በደረሰ የአውሮፕላን አደጋ 10 ሰዎች ሞቱ

አውሮፕላኑ የተከሰከሰበት ሥፍራ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በአሜሪካ አላስካ ግዛት አውሮፕላን ተከስክሶ አብራሪውን ጨምሮ 10 ሰዎች መሞታቸውን ባለሥልጣናት አረጋግጠዋል።

በበረዶዋማው ግዛት በደረሰው አደጋ ምክንያት የሞቱ ሰዎችን አስከሬን የማውጣት ሥራው መቀጠሉንም ገልፀዋል።

የብሔራዊ ትራንስፖርት ደኅንነት ቦርድ ሊቀ መንበር የሆኑት ጄኒፈር ሆሜንዲ የአደጋ መንስዔ ምን እንደሆ ለማወቅ ጊዜው "ገና ነው" ብለዋል።

ቤሪንግ ኤር የተባለው አየር መንገድ ንብረት የሆነው ሴስና ግራንድ ክራቫን አውሮፕላን ባለፈው ሐሙስ ነው ከራዳር ውጭ የሆነው።

ዘጠኝ ተሳፋሪዎች እና አንድ ፓይለት የጫነው አውሮፕላን ከአላስካ ምዕራባዊ ጠረፍ 55 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ኖም አካባቢ ነው የተከሰከሰው።

ከሟቾቹ መካከል ሁለቱ አላስካ ኔቲቭ ትራይብ ሄልዝ ኮንሶርሺየም የተባለው የእርዳታ ድርጅት ሠራተኞች ሲሆኑ ለሥራ ወደ ኖም እያቀኑ እንደነበር ድርጅቱ አስታውቋል።

ጄኒፈር እንደገለፁት ከዋሺንግተን ዲሲ የተላኩ መርማሪዎች እና ሌሎች ባለሙያዎች በአደጋው ሥፍራ ምርመራ እያደረጉ ይገኛሉ።

ሴስና የተባለው አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

"አሁንም አስከሬን የማውጣት ሥራው እንደቀጠለ ነው" ያሉት ጄኒፈር በአደጋው ምክንያት ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ላጡ ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝተዋል።

አካባቢው በረዶዋማ እና እጅግ ቀዝቃዛ በመሆኑ ምክንያት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሥራቸውን እያከናወኑ እንዳሉም አስታውቀዋል።

አውሮፕላኑ ደረቅ በረዶ ላይ መከስከሱንም ሊቀ-መንበሯ ጨምረው ተናግረዋል።

ቤሪንግ ኤር የተባለው አነስተኛ አውሮፕላኖች የሚያንቀሳቅስ አየር መንገድ በአደጋው የተሰማውን ሀዘን ገልፆ ከመርማሪዎች ጋር በትብብር እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።

የአላስካ ባለሥልጣናት አንድ አውሮፕላን ወደ ግዛቱ ከዘለቀ በኋላ ከራዳር ውጭ መሆኑ የተነገራቸው ሐሙስ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት 10፡00 እንደሆነ ተናግረዋል።

ከአደጋው ሥፍራ የተገኙ ፎቶዎች እንደሚያሳዩት በአየር ሁኔታው ምክንያት ሰማይ ጠቁሮ ነበር።

በአሜሪካ በቅርቡ ሌላ የአውሮፕላን አደጋ ተከስቶ 67 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።

በዋሺንግተን ዲሲ አሜሪካን ኤርላይንስ የተሰኘው አየር መንገድ ንብረት የሆነ አውሮፕላን አየር ላይ ሳለ ከሄሊኮፕተር ጋር ተጋጭቶ አደጋው መከሰቱ ይታወሳል።